Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በአፋር የችግኝ ተከላ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአፋር የችግኝ ተከላ አካሄዱ።

በችግኝ ተከላው የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባን ጨምሮ ሚኒስትሮችና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በዛሬው እለትም ብቻ በክልሉ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኝ እንደሚተከል ነው የተገለፀው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዘመቻን ቀደም ሲል በሃዋሳ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ያንንም ተከትሎ በሀገሪቱ የችግኝ ተከላው በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።

በዘንድሮው ዘመቻም 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአፋር ክልል በዱብቲ ወረዳ 700 ሄክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ የተዘጋጀውን የእንስሳት መኖ ማከማቻ ጎብኝተዋል።

ይህ ሥራ ከአራት ዓመታት በፊት አነስተኛ ስፋት ባለው የመሬት ይዞታ ላይ ይከናወን ነበር።

አርሶ አደሮቹ በአሁኑ ወቅት በየ45 ቀናት የሚታጨዱ ልዩ ልዩ የመኖ ሣር ዓይነቶችን በማብቀል ላይ ይገኛሉ።

ቆላማ አካባቢዎችን በመስኖ ለማልማት መንግስት የጀመረው ስራ አካል ነው እርሻው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከዚህ ቀደም በረሃማ አካባቢዎች ተብለው ሳይለሙ የቆዩ ቦታዎችን ወደ ስራ በማስገባት ከውጭ የሚገባ የግብርና ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን በጉብኝቱ ላይ ተናግረዋል።

እስካሁን የመስኖ አካባቢው ሶስት ጊዜ የለማ መሆኑን በማንሳት በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ጥጥ፣ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት አኩሪ አተር እና አሁን ላይ ደግሞ የእንሰሳት መኖ እየለማበት መሆኑን ነው ያስረዱት።

የአፋር ክልል ለጅቡቲ እና ለአሰብ ወደቦች በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ግብርናው የወጪ ንግድ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን ትኩረታችንን ሀገራችንን ማልማት ላይ ማድረግ አለብንም ብለዋል።

በህብረትና በጥረት ከሰራን ራሳችንን በመቻል ከሁለት እና ሶስት ዓመታት በኋላ ስንዴ ከውጭ አናስገባም ነው ያሉት።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘላቂ ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ ዛፍ እንዲተክል አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን ጨክነን መስራት ያለበን ዘላቂ ጥቅም እና ለሀገር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት ብለዋል።

በአልአዛር ታደለ

 
በአልአዛር ታደለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.