Fana: At a Speed of Life!

 ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የስልክ ውይይት አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት እና በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የስልክ ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱ የሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ግብፅ፣ ዚምባብዌ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ኬንያ መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀኔራል እንዲሁም፣ የአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ዳይሬክተር በስብሰባው ተሳትፈዋል።

እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎችን እና አፍሪካ ያጋጠሟት ፈታኝ ሁኔታዎች የውይይቱ አጀንዳዎች እንደነበሩም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ገልፀዋል።

የኮቪድ-19ን ቀውስ ለመቀልበስ የጋራ አመራር አስፈላጊ መሆኑ ላይ መሪዎቹ መስማማታቸውን ነው ያስታወቁት።

“ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ኢኮኖሚያችንን የማረጋጋት ሥራን ስንሠራ፣ የተቀናጀና ለአህጉራችን የሚበጅ አሠራር ያስፈልገናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በስልክ ውይይቱ ላይ በመሳተፍ በዚህ ፈታኝ ወቅት የአፍሪካ ቁርጠኛ አጋር በመሆን አሳይተዋል ያሏቸውን የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን አመሰግነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.