Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ተጠሪ ተቋማት የ10 አመት መሪ የልማት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ምክክር አካሄዱ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ተጠሪ ተቋማት የ10 አመት መሪ የልማት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ምክክር አካሄዱ፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ሀገራችን ከበለጸጉት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ የብልጽግና ተምሳሌት የመሆን የ10 አመት ራዕይና ግብ ይዛለች፡፡

ሀገራዊ የልማት ግቡን እውን ለማድረግ ብዙ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ተቋማቸውም ሰላምን፣ ደህንነትን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ መብትን በማክበርና በማስከበር እና የፍትህ አግልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ፍትሀዊ፣ ተደራሽ ማድረግ እና ተገማች መሆን እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በ10 አመቱ መሪ እቅድ ውስጥ የፍትህ አግልግሎትን የት ማድረስ እንዳለብን፣ ምን አይነት የፍትህ ተቋም፣ ባለሙያ እና የተቋም ግንባታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በእቅድ ውስጥ መካተቱን እና የሀገራችንን እቅድና ራዕይ ለማሳካት በግልጽነትና በባለቤትነት ስሜት ተጨማሪ ግብዓቶችን ማሰባሰብ የውይይቱ አላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ መሪ እቅድ የቀረበ ሲሆን ባለፉት አመታት የእቅድ አፈፃፀም መዝገቦችን የማስቀጣትና የመወሰን ምጣኔ፣ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የሰብዓዊ መብቶችን ከማስከበርና የሕግ ማሻሻያ ስራዎች በመስራት ስኬቶች መገኘታቸም ተገልጿል፡፡

የሕግ የበላይነትንና ልማትን የሚፈታተኑ ህገ ወጥ ተግባራትና የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መጨመር በበጀት አመቱ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ተጠቅሷል፡፡

ተቋሙ በ10 አመቱ መሪ እቅድ በ2022 በፍትህ አግልግሎት የአፍሪካ ፍትህ ተቋማት ተምሳሌት የመሆን ራዕይ በማስቀመጥ ራዕዩን እውን ለማድረግ የላቀ የሕግ ተፈጻሚነት፣ የፍትህ አግልግሎት አሰጣጥ እና የተቋም ግንባታ ስትራቴጂክ የትኩረት መስኮች ተቀርጸዋልም ነው የተባለው፡፡

የትኩረት መስኮችን ለማሳካት የወንጀል ስጋትን መቀነስ፣ የመንግስትና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ውጤታማነትን ማሻሻል፣ ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር፣ ለሕግ ተገዥነት ማሳደግን መሰረት ያደረጉ 10 ዋና ዋና ግቦች በመሪ እቅዱ መካተታቸውም ተነስቷል፡፡

በሃይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.