Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትናንት ከነበረበት በብዙ እጥፍ በተሻለ አቅም ላይ ይገኛል -ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢፌዲሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ የመጀመሪያ ዙር የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስነ ሰርዓቱ ወቅት ምሩቃኑ ዕውቀትን ሳያቋርጡ መፈለግና ለሌሎችም ማጋራትን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የዛሬው ምረቃ ለነገ ዕውቀትን ፍለጋ ሊያዘጋጃችሁ ያስፈልጋል፤ ዕውቀትን ሳትታክቱና ሳታቋርጡ እንድትሹ፣ ያገኛችሁትን ዕውቀት እንድታካፍሉ አደራ እላችኋለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትናንት ከነበረበት በብዙ እጥፍ በተሻለ አቅም ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷መከላከያ አሁን ያለበት ቁመና የኢትዮጵያ ጠላቶች እንኳን ለማሸነፍ ፤ ለመሞከርም የሚያሳስባቸው ነው ብለዋል።
መከላከያ እንደሚጠብቃት ሀገር ልክ ራሱን ማጠናከር እና ማዘመን ስለሚጠበቅበት በሁሉም መስክ ትልልቅ አቅሞችን እየገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚስትሩ ገልጸዋል ።
የመከላከያ የመጀመሪያ ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ነው ፤ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ደግሞ ራሱ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው ÷ኮሌጁ ብቁ የሆኑ የደህንነት እና የጸጥታ ተቋም አመራሮችን የማብቃት ጅምሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በደህንነት እና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ፋይዳ ያላቸውን ጥናትና ምርምሮች በማድረግ ሰፊ ፕሮጀክት ተነድፎ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል ።
በስልጠናው ከኢትዮጵያውን ባለፈ የጎረቤት ሀገራት ወታደራዊ ከፍተኛ መኮንኖችም አመራሮችም ተሳትፈው ተመርቀዋል።
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ በመጀመሪያ ዙር 38 ሰልጣኞች መመረቃቸውን ጠቁመው÷ከተመራቂዎቹ ውስጥ 10ሩ በደህንነት እና ስትራቴጂ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ናቸው ብለዋል።
በአላዛር ታደለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.