Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ለፕሬዚደንት ጆ ባይደን ግልጽ ደብዳቤ ላኩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወቅታዊ ሀገራዊና አህጉራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግልጽ ደብዳቤ ላኩ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለአሜሪካው ፐሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ በላኩት ደብዳቤ ላይ÷ ይህን መልዕክት በምንፅፍልዎ ሰዓት በህወሃት ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት ህጻናትና፣ እናቶችን ጭምሮ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በስቃይ ላይ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

እንዲሁም ይህ ደብዳቤ የተጻፈው÷ በትግራይ ክልል ያሉ ልጆቻችን በቅርቡ በሀገራችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‘አሸባሪ’ ብለን በፈረጅነው ድርጅት የጥይት ማብረጃ በተደረጉበት ጊዜ ላይ ሆነን ነው።

እንደ ኢትዮጰያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ከአሜሪካ የሚጠብቁት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማይገባ እና ከግለሰቦች ፍላጎት የጸዳ እንዲሆን ነው ብለዋል በደብዳቤያቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው እንደገለጹት በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራ ያካሄደው ህወሓት፥ ሆንብሎና አቅዶ በወሰደው የሃይል እርምጃ ህጻናትና እናቶችን ጨምሮ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንፁሃን ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

ቤተሰቦቻቸውን በግፍ ገድሎባቸዋል፤ ቤታቸው እንዲፈርስና ህይወታቸው እንዲመሰቃቀል አድርጓል፤ ሀብት ንብረታቸውን ዘርፏል፤ እንደ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን የመሳሰሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን አውድሟል ብለዋል።

በአገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ቅሬቶች በትግራይ የሚገኙ ህፃናትን ሳይቀር የጦርነት ሲሳይ እንዲሆኑ በጦር ሜዳ ውጊያ እንዲሰለፉ እያደረጓቸው እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በደብዳቤያቸው ያመለከቱት።

ይህም ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ ድርጊት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በትግራይ የሚገኙ ህፃናትና ወጣቶች በሌሎቹ የአገራችን ክልሎች እንዳሉት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉና ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዳይመሩ ይህ ቡድን ከፍተኛ እንቅፋት ከመፍጠር አልፎ እንደመነገጃ እንደሚጠቀምባቸውም አመልክተዋል።

አሸባሪው ቡድን በፈፀመባቸው አረመኔያዊ ግፍና ሰቆቃ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ህፃናትና እናቶችን ለቅሶና ዋይታ መስማት የተሳነው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፥ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያተኮረውን ያህል የአሸባሪውን ቡድን ድምጹን ለማሰማት አለመቻሉ ትክክልና ተገቢ አለመሆኑንም አመልክተዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ የአሜሪካ መንግስት የአሸባሪውን ቡድን ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ድርጊት በግልጽና በማያሻማ መንገድ ማውገዝ እንደነበረበትም አስምረውበታል።

ለአህጉሩ ሰላምና መረጋጋት በርካታ ጥረት በማድረግ ላይ ያለው በኢትዮጵያ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የፈጠረውን ጦርነትና ያደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋምና ለመታደግ የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ዕውቅና አለመስጠትና ከንቱ ለማድረግ መሞከር ፍትህ የጎደለው አካሄድ መሆኑን ነው ደብዳቤው የሚያስገነዝበው።

“የረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ወዳጅና ስትራቴጂያዊ አጋር የሆነው የአሜሪካ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሬ ላይ የያዘው አቋምና የሚከተለው ፖሊሲ ለኩሩዋ አገሬ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊነት ጉዳይም የዘለለ ነው”  ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም ከለውጡ በፊት የነበሩት ሶስት ዓመታት በዚህች ታላቅ ሀገር መነቃቃት የተፈጠረበትና በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለጭቆና አንገዛም ብለው በስልጣን ላይ የነበረውን ግፈኛ ድርጅት ያስወገዱበት ጊዜ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

“ህወሓት ያለፈበት ታሪክ እንደሚያሳየው ለራሱ የፖለቲካ ህልውና ሲል አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር በማጋጨት የስልጣኑን ጊዜውን ለማርዘም የሚፈጽመው ሴራ የእኔ አስተዳደር ሥልጣን በተረከበበት ጊዜ እንኳ አላባራም ነበር” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይልቁንም አሸባሪው የተጎጂነት ካባ ለብሶ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የሽብር አካላትን በገንዘብ እየደገፈ አለመረጋጋትን እየደገሰ ለመቀጠል ጥረት ሲደርግ መቆየቱን አውስተዋል።

በፕሮፖጋንዳና በሴራ የተካነው ይህ የጥፋት ቡድን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችንና ተቋማትን በእጅ አዙርና በቀጥታ በማሽከርከር ከ 3 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላትን ሀገር ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ይህ ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠት እውን ባይሆንም ፣ ኢትዮጵያ የተቀነባበረባትን ይህን ፈታኝ ወቅት ማለፏ አይቀርም፤ ይህንንም ጊዜ ታሪክ ይመዘግበዋል በማለት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ አገራችን ምርጫ የተወራውን ሟርት ሁሉ ተቋቁሞ ለአገሩ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ባሳየው ቁርጠኝነት የተነሳ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ 40 ሚሊየን የሚጠጉ የሀገሬ ሰዎች የተሳተፉበት ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዷል፡፡

በዚህም አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው።

ጠቅላይ ሚኒስቱሩ በደብዳቤያቸው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ የብልፅግና ፓርቲ እንዲያስተዳድረው ድምፅ መስጠቱን ገልፀዋል፡፡

ፓርቲዬ እና አስተዳደሬ ይህንን ኃላፊነት በእጁ ይዟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን የፍትሃዊ ልማት እምቅ አቅም ለማውጣት የበለጠ ቆርጠናል ነው ያሉት ።

እኛ ባለን አቅም ለተለያዩ ፍላጎቶች እና ጫናዎች ሳንሸነፍ ሕዝባችን የሚገባውን ክብር ፣ ደህንነት እና ልማት ለመስጠት የበለጠ ቆራጥ ነን ሲሉም ነው ያሰፈሩት ።

እናም ይህን የምናደርገው በዲሞክራሲና ፀጥታ ላይ ሰጋት በደገኑ ወንጀለኛ ድረጅቶችን በመጋፈጥ ነው ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ በብዙ የአለም ክፍል የሚከሰቱ ብሄራዊ ፣አካባቢያዊና፣ አለም አቀፋዊ የጸጥታ ስጋቶች ማስወገድ የአሜሪካ ዋና ፍላጎት ቢሆኑም የእርሶ አስተዳደር በ1980 በሶስተኛ ደረጃ በሽብረተኝነት ሊያስፈረጃው በሚችለው ህወሓት ላይ ጠንካራ አቋም አለመያዙ እስከአሁን መልስ ያጣ ጉዳይ ነው ሲሉም ነው የገለፁት፡፡

ኢትዮጵያ የአልሸባብን የሽብር ሥጋት ለመዋጋት የአሜሪካ ጠንካራ አጋር ሆና መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት በቀጠናው ላይ ጥላቻ ያለው ተመሳሳይ የሽብርተኛ ድርጅት እንደመሆኑ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጎን ትቆማለች ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።

የአሜሪካ ህዝብ፥ የአሜሪካን መንግስትን ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት የሚደግፈው መሰረቱ በዲሞክራታይዜሽን እሳቤ ሲሆን መታወቅ ያለበት ነገር መጠነኛ ማስተካከያ በማድረግ በባህል፣በታሪክ እና በተፈጥሮ ባለጸጋ በሆነች የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ ከሶስት ዓመት በፊት የዲሞክራሲ መንገድ የጀመረች ሀገር ናት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የአሜሪካ ህዝብ እና ቀሪው የምዕራቡ ዓለም በቀረበው ሪፖርት፣ትርክት፣ የመረጃዎች መጣረስ የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲይዙ ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእንደዚ አይነት ሁኔታ እንደኔ ያሉ ሀገራትን ከሚገባው በላይ ጎድቷል ብለዋል፡፡

ባለፉት ወራትም ተጎቺዎችን እንደ ጨቋኝ፣ ጨቋኞችን እንደ ተጎጂ በማድረግ ለአንድ ወገን ባደሉ እና በኔቶዎርክ በተሳሰሩ አካላት ሲተረክ ቆይቷል፡፡

ሁልጊዜ ታሪክ የሚያንጸባርቀው እውነትን መሰረት አድርገው ከቆሙት ጋር ነው፤ እኔም አምናለሁ እውነት በሂደት በዚህ ኩሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እየጠራች ትሄዳለች ብለዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካዊያን በዚህ ዓመት የእርሶን ወደ ፕሬዚዳንትነት መምጣት በበጎነት ሲያዩት ነበር፡፡

ይህ በጎ እይታ የመጣው የአፍሪካ እና የአሜሪካ ግንኙነት በ2021 አዲስ እይታዎችን ይዞ እንደሚመጣ በማመን፣ በስልጣን ዘመኖት የአፍሪካዊያኖችን ልዋላዊነት እና ግንኙነቱም የጋራ እድገት እና በመናበብ መሆን እንዳለበት ነው፡፡

አፍሪካዊያኖች ከ1950 ጀምሮ ቅኝ ግዛትን ሲቃወሙ ነበር፣ የሱ ትስስር ያለውን እና አዲሱን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትንም ላለመቀበል ትግላቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ኢትዮጵያም ከዚህ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ጋር ትልቅ ትግል ላይ ናት ነው ያሉት፡፡

እንደ የተባበሩት መንግስታት እና የፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችነቷ፣ ኢትዮጵያ ልጆቿ እና የአፍሪካ ልጆች አሁን ያጋጠማትን ችግር በጋራ በመቆም በማሸነፍ ትልቋን ሀገር ይታደጓታል፤ተከብራ እንደኮራች ትቀጥላለች፡፡

እንደ ኢትዮጰያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ከአሜሪካ የሚጠብቁት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማይገባ እና ከግለሰቦች ፍላጎት የጸዳ እንዲሆን ነው ብለዋል፡፡

የውጪ ፖሊሲ ከወሳኝ ፖሊሲ አውጪዎች እና ፖሊሲ ላይ ተጽህኖ ከሚያሳርፉ አካላት ነጻ ባለመውጣቱ፣ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር እንዲወዳጅ እና ግንኝነቱ ትክክል ባልሆነ ትርክት እንዲበላሽ ሆኗል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ውጤቱን በተደጋጋሚ እንዳየነው በአሜሪካ አስተዳደር በችኮላ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከማስተካከል ይልቅ በርካታ የአለም ህዝቦችን አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ከቷቸዋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምንም መልኩ ያኮረፉ ግለሰቦች ስልጣን ከሚሊዮኖች በላይ ሊሆን አይችልም፤ በዚህም ይህንን ኢትዮጵ ያ አትቀበልም ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያዊነታችንም እንደ አፍሪካዊነታችንም ይህ በኛ እንዲሆን አንፈቅድም ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል በደብዳቤያቸው፡፡

አባቶቻችን ለዘመናት በመላው አህጉሪቱ ያጋጠማቸው ውርደት፥ በአርንጓዴዋ መሬት፣ በወርቁ፣ በደማቅ ቀለም በተጻፈው ነጻነታቸውና ብዙዎችን ለስኬታማ ለነጻነት ያነሳሳ አህጉር ውስጥ አይደገምም ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.