Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ሕዝቡ መከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ የውስጡን ትንኮሳና የውጪውን ጫና እንዲመክት ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ እንደ ከዚህ በፊቱ እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ህልውና በመቆም የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክት ጥሪ አቀረቡ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፤

ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል።

ግጭት ላለማባባስ፥ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ስንል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል።

ሰላም የተወሰነ ዋጋ አንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ ዕድል ነው።

ድመት መገኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ጁንታው የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም፡፡ አሁን ባለው ቁመናው ያለ ግጭት ውሎ ማደር አይችልም።

ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት አየማገደ ይገኛል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ሕጻናት ወታደሮች የመታደግ ሞራላዊ ግዴታ ወድቆበታል።

ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም፡፡ ጁንታው የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው።

ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሳለን። በአንድ በኩል ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክከተን እንቀለብሰዋለን።

ጁንታው ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ በረሐብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲያላዝን ነበር። ለሕዝቡ ሲባል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ የረሐቡን አጀንዳ ትቶ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀመረ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ እርዳታና ስለ ረሐብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ ጁንታው ሕጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል።

የእርዳታ መግቢያ ኮሪደሮችን የግጭት ቦታዎች ሲያደርጋቸው የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመወቀስ ይቃጣቸዋል።

እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል።

ሕዝባችን ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከጠላት ፕሮፓጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ አሁንም ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

ጁንታውና አጋሮቹ ያላቸው ዐቅም ውሸትን መፈብረክ ብቻ ነውና። የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀናጅተው ሕዝብን ለመከፋፈል አየሠሩ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ሕዝባችን እንደ ከዚህ በፈቱ ሁሉ እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ህልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመከትና እንዲቀለብስ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.