Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በመላ ሀገሪቱ የኮቪድ-19 የምርመራ ዐቅም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮቪድ-19ን ለመከላከል የተቋቋመውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ ጠዋት ስብሰባ አካሂዷል።

እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፥ የክንውን ሂደቱም ተገምግሟል።

የጤና ሚኒስቴር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የገለፀ ሲሆን፥ 67 በመቶ የሚሆኑት አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆኑ፣ ቫይረሱ በማኅበረሰቡ መካከል መዛመቱን እንደሚያሳይም ተመላክቷል።

ቤት ለቤት የሚካሄደው የሙቀት ልኬት እና የቫይረሱን ምልክቶች የመለየት ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የመኖሩን ሂደት የሚፈትሹ ከ700 የሚበልጡ ቡድኖች በመላው ሀገሪቱ መሰማራታቸው ነው የተገለፀው።

የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ንዑስ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ የመንግሥት ተቋማት በአካል ተገናኝተው በሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች ምትክ የሚከናወኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስብሰባዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆኑን አንስቷል።

በ11 ተቋማት ውስጥ ለወትሮው ገጽ ለገጽ የሚሰጡ 75 መንግሥታዊ የሆኑ አገልግሎቶችም፣ አሁን በኢንተርኔት በመታገዝ እየተካሄዱ ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ፣ ሌሎቹም ንዑሳን ኮሚቴዎች ዋና ዋና ክንውኖችን እንዲሁም ተግዳሮቶችን የገለጹ ሲሆን፥ በተለይም በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ትኩረት ተደርጎበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመላው ሀገሪቱ የምርመራ ዐቅም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በተጨማሪም፣ ወረርሽኙን ከመመከት ጎን ለጎን፣ በዐበይት ዘርፎች ምርታማነትን ማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነም ነው የተናገሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.