Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለአፍሪካ ህብረት ሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለአፍሪካ ህብረት ሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ከለውጡ በፊት የተከሰተውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አስረድተዋል፡፡
ሕዝባዊ እንቅስቃሴውንም ተከትሎ የመጣውንም ለውጥ ለማደናቀፍ ሕወኃት ሃገሪቷ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እዚህም እዚያም ሲፈጥር መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
የጥፋት ኃይሉ ከኢትዮጵያ ባሻገር የቀጠናውን ሰላም ለማወክ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ውጪ ምርጫ ማካሄዱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷በክልሉ ውስጥ መደበኛ ያልሆነ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ሲያሰለጥን መቆየቱንም ነው የገለጹት፡፡
በመጨረሻም ጥቅምት 24 ላይ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ቡድኑ ጥቃት መሰንዘሩን አስረድተዋል ፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎም መንግስት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ህግ የማስከበር ዘመቻ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
የህግ ማስከበር ዘመቻውም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የፌደራል መንግስቱ እስካሁን ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች 84 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ መቅረቡን ነው የጠቀሱት፡፡
ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አክሱምን ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የራሱን ገለልተኛ ምርመራ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት ከሚመለከታቸው የተባበሩት መንግስታት ተቋማት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህብረት ሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራዎችን እንዲያካሂድ ፈቃዳችንን እንገልፃለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመጨረሻም የአፍሪካ ህብረት በአስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-

https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.