Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የሮሃ የህክምና ማዕከል ሜጋ ፕሮጀክት ግንባታን አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሮሃ የህክምና ማዕከል ሜጋ ፕሮጀክት ግንባታን አስጀመሩ፡፡

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ወቅት ፕሮጀክቱ በከተማዋ ተበታትነው የነበሩ ፕሮጀክቶችን የሚሰበስብ መሆኑን ጠቅሰው፥ በህክምናው ዘርፍ የሚመረቁ ዜጎችን የስራ ባለቤት ለማድረግ ያግዛልም ብለዋል።

ጤናን ለመጠበቅ በከተማዋ ትልልቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከላት (ጂም) እንዲገነቡ የከተማ አስተዳደሩ ሁኔታዎችን እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።

ፕሮጀክት የመጀመር ችግር የለብንም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢንቨስትመንት ግሩፑ በገባው ቃል መሰረት ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ትኩረት እንዲሰራ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የሮሃ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ዋሽንግተን የኢትዮጵያ መንግስት በዘርፉ እንዲሳተፉ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆስፒታሉ ግንባታ በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ሁሉም ሆስፒታሎች በአምስት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሏል።

ማዕከሉ የካንሰር፣ የሴቶች እና ህጻናት፣ የንቅለ ተከላ እና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል።

በዚህም በማዕከሉ የህክምና አገልግሎት ከሚያገኙ ዜጎች መካከል 10 በመቶዎቹ በሪፈራል ከመንግስት ሆስፒታሎች የሚመጡ ይሆናሉ ነው የተባለው።

የህክምና ማዕከሉ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ባሻገር ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት የሚያስችል የትምህርት ማዕከልም እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ12 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ሲሆን፥ የግንባታ ወጪው በሮሃ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚከናወን ነው።

የህክምና ማዕከሉ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከ1 ሺህ 200 አልጋ በላይ ያላቸው 5 ሆስፒታሎች ይኖሩታል።

የህክምና ማዕከል ግንባታው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የህክምና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።

ማዕከሉ ጥንታዊ የኢትዮጵያን የኪነ ህንጻ ዲዛይን ተከትሎ የሚገነባ ነው ተብሏል።

ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ4 ሺህ 200 የህክምና ባለሙያዎች ከሚፈጥረው የስራ እድል በተጨማሪ በግንባታው ወቅት ለ7 ሺህ 500 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በምስክር ስናፍቅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.