Fana: At a Speed of Life!

ጥምቀትን በዓለም ቅርስነት ለማቆየት በሚገባው ልክ ልንጠብቀው ይገባል- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥምቀት በዓል በጎንደር በድምቀት ተከበረ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክትም የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ በመመዝገቡ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ 4 የማይዳሰሱ ቅርሶቿን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ፥ ሌሎች ቅርሶችን ለማስመዝገብም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ጠቃሚ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ ለዚህ የበቃችበትን ሚስጥር ማወቅ ተገቢ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ሚስጥሩ እነዚሀን ቅርሶች በተገቢው መንገድ ጠብቆ ማቆየት መቻል መሆኑንም አንስተዋል።

ቅርሶቻችን የማንነታችን መሰረቶች ናቸውና በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባህሉን እንዲጠብቅ ሊደረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ዘለዓለማዊ እንዳይደለ እና በዚያው ደረጃ ቅርሶቹን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባም አንስተዋል።

በመሆኑም ጥምቀትንም ሆነ ሌሎች የዓለም ቅርሶች መጠበቅ የእያንዳንዱ ሃላፊነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የጥምቀት በዓል በጎንደር በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ላደረጉ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ወጣቶችና ከሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችና ከውጭ የበዓሉን ስነ ስርአት ለመታደም በጎንደር ለተገኙ ምዕመናን ምስጋና አቅርበዋል።

በጎንደር ጥምቀተ ባህር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ፥ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰው እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።

በጎንደር ከተማ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት ሀይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ነው የጥምቀት በዓል ተከብሯል።

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.