Fana: At a Speed of Life!

ጨፌ ኦሮሚያ 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ የስራ ዘመን 6ኛ ዓመት 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአዳማ እያካሄደ ነው፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባዔ ሎሚ በዶ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ህወሓት የሰላም አማራጮችን በመተው ራሱን ያጠፋበትን የማይሆን መንገድ መርጧል ብለዋል፡፡

ከጥፋ ቡድኑ ስንብት በኋላ መንግስት ህዝቡን አስተባብሮ ወደ ልማት ፊቱን አዙሯል ነው ያሉት፡፡

አፈ ጉባዔዋ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጨፌ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ስለመሆኑ ጨፌው አፅንዖት መስጠት እንዳለበት ጠቅሰው፥ የድል በዓሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጁንታውን ድል ባደረገበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ጨፌው ባለፉት ስድስት ወራት በስራ አስፈፃሚው የታቀዱ ስራዎች በአግባቡ መሰራት አለመሰራታቸውን በተመለከተ ክትትል ሲያደርግ ነበርም ብለዋል፡፡

ለአብነትም በዜግነት አገልግሎት የተሰሩ ስራዎች አበረታች ነበሩ ያሉት አፈ-ጉባኤዋ፤ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ምርጫ 2013 ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ጨፌው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ህዝብን ባሳተፈና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ በልማት፣ በሰላም እና በመልካም አስተዳደር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡

የስራ እቅዶቹን በማስፈፀም ሂደት የሰላምና መረጋጋት እጦት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት እና ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ተግዳሮት የፈጠሩ ቢሆንም የክልሉ ህዝብና መንግስት በፈጠሩት ቅንጅት እና ባደረጉት ጠንካራ ርብርብ ስራዎቹ ስኬታማ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን በማሳካት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከተው ሁሉ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጉባዔው የ2013 ዓ.ም የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ይገመገማል፡፡

በተጨማሪም የኦሮሚያ የቤቶች ልማት አስተዳደርና ማስተላለፍ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ የውሀ ኃብት ልማት፣ የግብርና ምርት ጥራት ቁጥጥር፣ ስታቲስቲክስ፣ የመአድን ኃብት ልማት እና የክልሉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለማሻሻል የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል፡፡

እስከ ነገ በሚቆየው ጉባኤውም የተለያዩ ሹመቶችን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.