Fana: At a Speed of Life!

ፈረንሳይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ፓሪስን ጨምሮ በስምንት ከተሞች የሰዓት እላፊ ልትጥል ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፈረንሳይ በሀገሪቱ ዳግም እያገረሸ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ፓሪስን ጨምሮ በስምንት ከተሞች የሰዓት እላፊ ልትጥል ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዳስታወቁት የምሽት የሰዓት እላፊ ገደቡ በሀገሪቱ ዳግም እያገረሸ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ያለመ ነው።
ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ማለዳው12 ሰዓት የሚቆየው የሰዓት እላፊ ገደብ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የታወጀው የሰዓት እላፊ ገደብ ለአራት ሳምንታት የሚቆይ መሆኑንም ነው የገለፁት።
ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ የህብረተሰብ ጤና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁም ነው የተነገረው።
በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ዳግም እያገረሸ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።
ከእነዚህ ውስጥ ጀርመን አንዷ ስትሆን፥ በሀገሪቱ የሚገኙ እና ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ የስጋት ስፍራ በሚል የተለዩት ምግብ ቤቶች እና የመጠጥ ቤቶች በጊዜ እንዲዘጉ ትዕዛዝ አሳልፋለች።
የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ትዕዛዙ ከትናንት ጀምሮ ተፈፃሚ እንዲሆን ውሳኔ ያሳለፉ ሲሆን፥ ሀገሪቱ ከውሳኔው ላይ የደረሰችው ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተከትሎ ነው።
ሀገሪቱ ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ እንዳይሰባሰቡ የከለከለች ሲሆን፥ የምሽት የመዝናኛ ክበቦች እና መጠጥ ቤቶችም በጊዜ በራቸውን እንዲዘጉ ትዕዛዝ አሳልፋለች።
ኔዘርላንድስም በከፊል ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በማድረግ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች ሲሆን፥ ምግብ ቤቶች እና ካፊቴሪያዎችንም በመዝጋት ላይ መሆኗ ተገልጿል።
የስፔኗ ካታሎኒያ ምስራቃዊ ክልልም ከዛሬ ጀምሮ ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ለ15 ቀናት ዝግ እንዲሆኑ ወስናለች።
ቼክ ሪፐብሊክም ትምህርት ቤቶች እና መጠጥ ቤቶችን የዘጋች ሲሆን፥ የአየርላንድ መንግስትም የሰዎችን ቤት ለቤት መጠያየቅን መከልከሉ ተነግሯል።
ምንጭ፦ bbc.com
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.