Fana: At a Speed of Life!

ፌስቡክና ኢንስታግራም የጀኔራል ሱለይማኒን ሃሳብ የሚደግፉ መረጃዎችን ከገጻቸው እያስወገዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢንስታግራም እና ፌስቡክ በአሜሪካ የተገደሉትን የኢራኑ ጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒን ሃሳብ የሚደግፉ መረጃዎችን ከገጻቸው እያስወገዱ ነው።

የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ መተግበሪያዎቹ መረጃዎቹን ከገጸቸው የሚያስወገዱት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ተከትሎ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ደንበኞች የጀኔራል ሱለይማኒን ሃሳብ ደግፈው በመተግበሪያዎቹ የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች እያስወገዱ መሆኑ ተመላክቷል።

በተለይም በኢራን የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጄኔራሉን ደግፈው የሚያሰራጩትን መረጃ ከገጻቸው እያስወገዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህን ተከትሎም ኢራናውያን ኢንስታግራም እና ፌስ ቡክ በፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢራን መንግስት ቃል አቀባይ አሊ ሬቤይ በበኩላቸው፥ ድርጊቱን ዴሞክራሲያዊ አሰራርን ያልተከተለ እና ሃላፊነት የጎደለው ሲሉ ኮንነውታል።

የኢራኑ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ በኢራቅ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ በሀገራቱ መካከል ውጥረት መንገሱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው በተለያዩ ኢራናያውያን ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ኢንስታግራም እና ፌስ ቡክም አሜሪካ ማዕቀብ በጣለችባቸው ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሲተዳደሩ የነበሩ ገጾችን ከመተግበሪያቸው ማስወገዳቸውን አስታውቀዋል።

ምንጭ ፥ ሲ ኤን ኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.