Fana: At a Speed of Life!

ፌደራል ፖሊስ እያከናወነ በሚገኘው የለውጥ ስራ ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን “ከራስ በላይ ለሀገርና ለህዝብ! ” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።
የፓናል ውይይቱ ነገ የሚያከብረውን በዓል አስመልክቶ ነው በሸራተን አዲስ ሆቴል እያካሄደ የሚገኘው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የተለያዩ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮችና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በእዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የፖሊስ ተልዕኮ ከጊዜ ወደጊዜ እየከበደና በውስጥም በውጭም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየገጠሙት መሆናቸውን ጠቅሰው÷ እነዚህን ችግሮች መፍታት በሚያስችል መልኩ ተቋሙን የመለወጥ ሥራ በጥናት እየተካሄደ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የለውጥ ሥራው መጀመሩን አመልክተዋል።
በዚህም በአደራጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የነበሩበት ችግሮች እየተፈቱ ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ለማስቀጠልና የህግ የበላይነት እንዲከበር የበለጠ እንደሚሰራም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው አረጋግጠዋል።
የክልል መንግስታት ለእዚህ የሚመጥን የሰው ኃይል ግንባታ ላይ የድርሻችውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የተጓዘበትን ሂደት የሚያሳይ ዶክመንተሪ ፊልም ለታዳሚዎች ቀርቧል።
በቀጣይም የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እንደሚደረግበትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ለፖሊስ መልዕክትና የሥራ መመሪያ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.