Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በአቶ ልደቱ ላይ ክስ እስከሚመሰርት መርማሪ ፖሊስ እንዲሰጠው የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ ውድቅ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው ላይ ፖሊስ  ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ ማጠናቀቁን  ገልፆ  አቃቤ ህግ ክስ እስከሚመሰርት ድረስ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም ሲል ውድቅ አደረገ።

ፍርድ ቤቱ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ መዘጋቱን ገልፆ  አቶ ልደቱ አያሌው በሌላ መዝገብ የዋስትና ጥያቄያቸውን  እንዲያቀርቡ አዟል።

ለአራተኛ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው ”ፍርድ ቤቱ የጤናዬን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፣  ከዚህ በፊት ያቀረብኩት የህክምና ማስረጃ የልብ ህመምተኛ መሆኔን  ተከትሎ ለኮቪድ-19  ወረርሽኝ ተጋላጭ እንደሚያደርገኝ ተጠቅሶ የተፃፈ ቢሆንም፥ በፖሊስ ጣቢያ የኮቪድ-19 ምርመራ አልተደረገም፣  ጤናዬን  ከግምት ውስጥ ያስገባ ርቀትን የጠበቀ አያያዝ አልተደረገልኝም፣ በተጓዳኝ ደግሞ በአንድ መፀዳጃ  ቤት 50 እስረኞች እንደሚጠቀሙና ይህም ለጤናዬ አደጋ ነው‘ ብለዋል።

”ፖሊስ እስከ ዛሬ ሲያከናውን የነበረው ምርመራ አዲስ ውጤት ያልታከለበት፣ አስተባብረሃቸዋል የተባሉ ተባባሪዎች ያልተያዙበት እና ምስክሮቼ ያልቀረቡበት  ነው‘ ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።

ፖሊስም እስካሁን ሲያከናውን የነበረው ምርመራ በእጃቸው ላይ የነበሩ የስልክ መልዕክቶችን  እንዲሁም በእጃቸው ላይ የተገኘ የሽግግር መንግስት መመስረቻ ሰነዶች  ውጤትን በመዝገቡ ማካተቱን  ገልፆ፥ ይሁንና ”ምርመራዬን  አጠናቅቂያለሁ፣  ይህም መዝገቡንም አቃቤ ህግ መርምሮ  ክስ እስከሚመሰርት  ድረስ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ‘ ሲል  ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም  ”በዚህ መዝገብ ላይ ምርመራ መጠናቀቁን  በመግለፅ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት  ህግ አንቀፅ 59 1 እና 2 መሰረት ያቀረብከው ጥያቄ አግባብነት የሌለውና ያጠናቀከው መዝገብ ተጨማሪ ጊዜ የማያሰጥ ነው፣ ጥያቄህም የህግ አግባብነት የለውም‘ ሲል ውድቅ አድርጎበታል።

ይሁንና በዛሬው ዕለት በሁለት ጠበቃ ተወክለው የቀረቡት አቶ ልደቱ  አያሌው የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ በዚህ የተዘጋ መዝገብ ሳይሆን በሌላ መዝገብ ማቅረብ ይችላሉ  ሲል የመርማሪ ፖሊስ መዝገብን ዘግቷል።

 

በታሪክ አዱኛ

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.