Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ ጃዋር ላይ ቀሪ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14ቱም ተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ከአራተኛ እስከ 9ኛ  የተዘረዘሩ ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸውን የሚገልፅ ውጤት ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።

ከዚህ በፊት አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ከጓደኞቻቸው ጋር መገናኘት አልቻልንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ በጓደኛ የመጠየቅ  መብት ቢኖራቸውም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለም።

አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር ከልጄ እና ከባለቤቴ ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንድገናኝ ይፈቀድልኝ  ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በሳምንት ሁለት ጊዜ በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲገናኙ አዟል።

ጆሮዬን ታምሚያለሁ የተሻለ ሆስፒታል ልታከም  ብለው አቤቱታ ያቀረቡት 12ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሸምሰዲን ጣሃ በመረጡት ሆስፒታል እንዲታከሙ እንዲመቻችላቸው አዟል።

ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ ቀሪ ምስክሮችን ለማድመጥ ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል በተጠረጠሩት ከበደ ገመቹ እና አብዲ ዓለማየሁ ላይ አቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰርት የ15 ቀን ጊዜ ሰጥቷል።

ፖሊስ ምርመራዬን አጠናቅቂያለሁ ብሎ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ አስረክቧል።

በችሎቱ አንደኛው ተጠርጣሪ አብዲ ዓለማየሁ አርቲስት ሃጫሉ በተገደለበት ወቅት በቦታው አልነበርኩም ያለ ቢሆንም ሌላኛው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያሚ በበኩሉ አርቲስቱ ሲገደል ከበደ ገመቹ እና አብዲ ዓለማየሁ አብረውት እንደነበሩ አስረድቷል።

በዚሁም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል የአስራት ሚዲያ ባለሙያዎች ላየ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት የአዲስ አበባ አስረኞች አስተዳደር ሀላፊ ቀርቦ በተጠርጣሪዎቹ የጤና ሁኔታ እና የእስር አያያዝ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በዚህም የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገላቸው እና ነፃ መሆናቸውን አስታውቋል።

ይሁንና ተጠርጣሪዎቹ በፅዳት እጥረት ለጤና ችግር እየተጋለጥን ነው ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ከዐስር ሲፈቱ በጤናቸው ላይ እክል አጋጥሞ ጠባሳ ይዘው መውጣት የለባቸውም፣ ፖሊስ ትእዛዝ እስከሚሰጠው ድረስ መጠበቅ የለበትም፣ ደህንነታቸው እና ጤንነታቸው በተጠበቀ ቦታ ሊቆዩ ይገባል ሲል ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፖሊስም ምርመራውን አጠናቆ እንዲመጣም ተጨማሪ ሰባት ቀን ፈቅዷል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.