Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ አርቲስት ሃጫሉ ሲገደል  አብራው በነበረችው ላምሮት ከማል ላይ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20፣ 2012 (ኤፍ. ቢ.ሲ) በሰኔ 22 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ በገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ  አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሲገደል  አብራው የነበረችው ላምሮት ከማል ላይ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ ፈቀደ።

መርማሪ ፖሊስ ጉዳዩን ለተመለከተው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት  ምርመራ ማጠናቀቁን ገልፆ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ አስረክቧል።

አቃቤ ህግም በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህግ 109 መሰረት 15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዋ በበኩሏ “አርቲስት ሃጫሉ ጓደኛዬ ነው፣ በወቅቱም አብሬው ነበርኩ፣ ይህንን አልክድም፣ ለህይወቴ ሳልሳሳ ወንጀለኞቹን አሳይቻለሁ፣ ፍርድ ቤቱ የቤተሰቦቼ ማህበራዊ ህይወት እንዳይሰተጓጎል  በዋስ ይልቀቀኝ” ስትል ጠይቃለች።

ፍርድ ቤቱም በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህግ 63 መሰረት ጉዳዩ የግድያ ወንጀል የተፈፀመበት በመሆኑና ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክስ ሲመሰረት ከ15 ዓመት በላይ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ ዋስትና የሚያስከለክል ነው በማለት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።

ነገር ግን አቃቤ ህግ በ15 ቀን ውስጥ ክስ ካልመሰረተ የዋስትና ጥያቄ አቤቱታን ማቅረብ ይቻላል ብሏል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.