Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ ዛሬ የእነ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ መውጫን ጨምሮ አምስት መኮንኖች ጉዳይ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፍርድ ቤቱ ዛሬ የእነ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ መውጫን ጨምሮ የአምስት መኮንኖች ጉዳይ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ብርጋዴል ጄኔራል አብርሃ መውጫ ፣ኮሎነል ገብረህይወት ደስታ፤ ኮሎነል ዩሃንሰ በቀለ እና ኮሎነል ዘነበ ታመነ እና ሻለቃ ገ/እግዛብሄር ግርማይ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ቀናት  ውስጥ በተጠረጠሩበት ህገመንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል  የሰራውን የምርመራ ስራ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

በዚህም በርካታ የምርመራ ስራ ማከናወኑን ነው መርማሪ ፖሊስ የገለጸው።

ተጠርጣሪዎቹ ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ በጋራ በመደራጀት በሰሜን ዕዝ ጥቃት ለመፈጸም ሲሰሩ እንደነበር በቴክኒክና በሰበሰብኩት የሰው ማስረጃ ማረጋገጥ ችያለሁ ሲል አብራርቷል።

በተለይም 1ኛ ተጠርጣሪ ብርጋዴል ጄኔራል አብርሃ መውጫ ከአራቱ ተጠርጣሪዎች ጋር በጋራ ሰሜን እዝ ጥቃት እንዲፈፀም ሲንሳቀስ እንደነበረ አረጋግጫለው ያለ ሲሆን፤

2ኛ ተጠርጣሪ ኮሎነል ገብረሂወት ደስታ የሰሜን እዝ ሬዲዮ ኔትዎርክን በማቋረጥ እዙ እንዲመታ ማድረጋቸውን በ6 የሰው ምስክሮች አረጋገጫለው ሲል ተናግሯል።

በተራ ቁጥር 3 ላይ የተጠቀሱት ኮሎነት ዩሃንስ በቀለ በተመለከተ መርማሪ ፖሊስ በተሰጣቸው ተልዕኮ የሰሜን እዝ እንዲመታ ማድረጋቸውን በስምንት የሰው ምስክር አርጋግጫለው ብሏል ።

በተራ ቁጥር አራት ላይ ለተጠቀሱት ኮሎነል ዘነበ ታመነን በተመለከተም መርማሪ ፖሊስ የሰሜን እዝ ኔትዎርክን በማቋረጥ እዙ እንዲመጣ ማድረጋቸውን በ5 የሰው እና በቴክኒክ ማስረጃ አረጋግጫው ነው ያለው ፖሊስ።

ይሄው ተጠርጣሪ ስልጣኑን ተገን በማድረግም ወታደሮች ትግራይ ሄደው በድብቅ አሰልጥነው እንዲመጡ ከመንግስት በጀት አበል እየከፈለ  እንደነበረም ባደረኩት ምርመራ መረጃ አግኝቻለሁ።

በተራ ቁጥር ስድስት ላይ የተጠቀሱት  ሻለቃ ገ/እግዛብሄርን በተመለከተ በተመሳሳይ ተግባር ተሳትፈው እንደነበረ በአራት የሰው ምስክርና በቴክኒክ ማስረጃ አረጋግጫለው ሲል ለችሎቱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ከተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በፍርድ ቤት በተደረገ ብርበራ አንድ ክላሽ መሳሪያ ከ88 ጥይቶች ጋር እና ሽጉጥ ከ8 ጥይት ጋር መገኘቱ የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ከጀመርኩት ሰፊ ምርመራ አንጻር የወንጀሉን ውስብስብነትና ስፋት ከግምት ውስጥ ገብቶ ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በማስረዳት ተደጋጋሚ ለምርመራ በሚል ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተቃውመው ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም በዋስ እንዲለቃቸው ጠይቀዋል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ መድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ በርካታ ምርመራ ማድረጉን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን ገልጾ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠዋት በነበረው ችሎት በእነ ኮሎነል ፍስሃ በየነ መዝገብ አምስት መኮንኖችም ጉዳያቸው ታይቷል።

ተጠርጣሪዎቹ   ኮሎነል ፍስሃ በየነ ፣ ኮሎነል ሃይላይ መዝገቡ ፣ ሌተናል ኮሎነል ሙዘይ ተሰሜ፣ ኮሎነል ሰመረ በርሄ እና ሌተናል ኮሎነል ባራኪ ጡማሎው  ናቸው።

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታዩት።

ተጠርጣሪዎቹ በስራ ላይ በነበሩበት ጊዜ  ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ከተባሉ ጸረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል የመናድ ሙከራ እና የሃገር ክህደት ወንጀል  ተጠርጥረው ምርማራ እየተከናወነባቸው እንደሚገኙ ያታወቃል።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ የሰራውን ምርመራ ስራ ለችሎቱ አብራርቷል።

በዚሀም  ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ በመንግስት በጀት ህወሓት ለዚህ ወንጀል የመለመላቸውን ወታደሮች ትግራይ ክልል ሄደው በድብቅ ማሰልጠናቸውን ማስረጃ ማቅረቡን ፖሊስ አስታውቆ ነበር፡፡

ይህንን ማስረጃ ለማጠናከር የምርመራ ቡድን ወደ መቀሌ እንደላከና  የስልክ ልውውጦች እንዲላክለት ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ደብዳቤ ተልኮ ምላሽን እየተጠባበቀ እንደሆነ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ዛሬ በመንግስት ጠበቃ ተወክለው የቀረቡት 1ኛ ተጠርጣሪ ኮሎነል ፍስሃ በየነ እና ሶስተኛ ተጠርጣሪ ሌተናል ኮሎነ ሙዘይ ተሰሜ በጠበቃቸው አማካኝነት ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃ መርማሪ ፖሊስ ባለመቅረቡ በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በተለይም ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በመንግስትና በፍርድ ቤቱ ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች ተጠርጣሪዎች በብሄራችን ምክንያት ነው የታሰርነው ሲሉ ላቀረቡት መቃወሚያ ፖሊስ ማንም በብሄሩ የታሰረ የለም በወንጀል ተሳትፎው ፤ ማንኛውም ሰው በወንጀል ከተጠረጠረ ይታሰራል ሲል ምላሽ ሰቷል።

ችሎቱም መዝገቡን መርምሮ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ 12ቱን ቀን ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.