Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ዝግጁ  መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን ፍርድ ቤቶች ገለጹ።

መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ስራ ገብቷል።

አዋጁን ተከትሎ የወጣው የማስፈፀሚያ ደንቡ በአራት ዋና ዋና ከፍሎች ክልከላን በማስቀመጥ፤ ግደታዎችን በመጣል፤ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን በመዘርዘር ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን  አስቀምጧል፡፡

በዚህም የፌደራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችም መደበኛ የወንጀል ዳኝነት አስራር ስርዓትን ለጊዜው በማቆም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ስራቸውን እንዲያከናውኑም ተደንግጓል።

በተለይም በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎች በተቋማትና ድርጅቶች ሲጣሱ ግለሰቦችም አዋጁን ሲተላለፉ ፍርድ ቤቶቹ በህግ ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ከሆኑት መካከል ፍርድ ቤቶች ለአዋጁ ተፈጻሚነት ያላቸውን ዝግጁነት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል፥ መንግስት የዜጎቹን ህልውና ለመጠበቅ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆን በቅድሚያ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ይሁንና ይህ አዋጅ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚቀሳቀሱ በተለይም አዋጁን ተላልፈው የተገኙ ሰዎችን በህግ በተቀመጠው የቅጣት አወሳሰን መሰረት በዳኝነት አካሉ ፈጣን እልባት ለመስጠት በፍርድ ቤቶች በኩል ዝግጁነት እንዳለ አረጋግጠዋል።

በተለይም የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በፍርድ ቤቶች ተረኛ ችሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደራጁ በማድረግ በአዋጁ አተገባበር ዙሪያ የሚገጥሙ መተላለፎችን በህግ መሰረተ ተፈፃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ፉአድ ኪያር አህመድ በበኩላቸው፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 ጀምሮ በከፊል የተዘጉና በተረኛ ችሎት ለውሳኔ የደረሱ እና ውዝፍ መዛግብት ላይ ውሳኔዎችን እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለአስቸኳይ አዋጁ ተፈጻሚነት ግን ፍርድ ቤቱ ዝግጁ ነው ያሉት አቶ ፉአድ፥ የህግ እልባት የሚሹ ጉዳዮች ሲያጋጥሙም በተረኛ ችሎት በመመልከት አፋጣኝ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነት መኖሩንም ተናግረዋል።

በታሪክ አዱኛ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.