Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲው ድክመቶቹን አርሞ ለመውጣት ጠንካራ ግምገማ አካሂዷል- አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ባለፉት ሁለት ቀናት ባካሄደው ስብስባ ድክመቶቹን አርሞ ለመውጣት ጠንካራ ግምገማ ማካሄዱን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል።
 
ፓርቲው በሁለቱ ቀናት ቆይታው ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ በኋላ በኢኮኖሚ፣ በማህበራና በፖለቲካዊ መስኮች የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የጀመሩ ውጤቶች መመዝገባቸው ተነስቷል።
 
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ታረቀኝ ÷ ፓርቲው ድክመቶቹን አርሞ ለመውጣት ጠንካራ ግምገማ አካሂዷል ብለዋል።
 
በተለይም የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
 
በዚህ መሰረት አቶ ለማ መገርሳ፣ ወይዘሮ ጠይባ ሃሰንና ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መታገዳቸውን ገልጸዋል።
 
አቶ ለማ መገርሳ ወደፊት በመውጣትና በመታገል በለውጡ ውስጥ የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው ÷ ለዚህም ጉባኤው እውቅና መስጠቱን አንስተዋል።
 
ነገር ግን የፓርቲ ውህደት በተፈጸመ ማግስት የፓርቲውን ህግ ባላከበረ መልኩ በሚዲያ መግለጫ ሰጥተዋል ብለዋል፡፡
 
መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ነባር የኦዲፒ ስራ አስፈጻሚዎችና ነባር ታጋዮች አንድ ላይ በመምጣት የተገመገመበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው÷ በወቅቱም አቶ ለማ መገርሳ ስህተት መሆኑን አምነዋልም ነው ያሉት።
 
ከዚህ ባለፈም በወቅቱ አቶ ለማ የድርጅቱን የስነ ምግባር ደንብ አክብረው ለመንቀሳቀስ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
 
ሆኖም ከዚያ ወዲህ በተደረጉ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባዎች ላይ ባለመገኘት፣ መገኘት በሚገባቸው መንግስታዊ ሃላፊነቶች ላይ ሳይገኙ በመቅረት፣ በጨፌ ኦሮሚያ ስብሰባ ላይ ባለመገኘት እንዲሁም ለሁለት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም አለመገኘታቸውን ጠቁመዋል።
 
ድርጅቱ ውስጥ ትልቅ ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሳለ ልዩነት እንኳን ቢኖር በድርጅታዊ አሰራር መጥተው ሀሳባቸውን ማቅረብና ልዩነቶቻቸውን ማስመዝገብ ሲችሉ ያ ሳይሆን መቅረቱንም ነው አቶ ታረቀኝ የተናገሩት።
 
ስለሆነም አቶ ለማ ከአባልነት ታግደው እንዲቆዩ በስብሰባው በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስረድተዋል።
 
ወይዘሮ ጠይባ ሃሰንም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ ሲደረግ በነበረ ግጭት ውስጥ ስማቸው ሲነሳ መቆየቱን ጠቁመው ÷ ከፍተኛ አመራሩና አባሉም አመኔታ በማጣቱ ጥያቄ ያነሳ ስለነበር ጉዳያቸው እስከሚጣራ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲታገዱ መደረጉ ተገልጿል።
 
ዶክተር ሚልኬሳ ሚዳጋም ከፓርቲው ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ በውስጥ ማድረግ የሚገባን ትግል ወደ ውጭ በማውጣት እና መገኘት በሚገባቸው ስብሰባዎች ላይ ባለመገኘት ታግደው እንዲቆዩ እርምጃው ተወስዷልም ነው ያሉት።
 
አቶ ታረቀኝ ፓርቲው በቀጣይ ከህዝቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተናግረው÷ ህዝቡም ከጎኑ እንዲሰለፍ ጠይቀዋል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.