Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮን ተቀብለው አነጋገሩ።
 
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከውይይቱ በኋላ እንደተናገሩት፥ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ማይክ ፖምፒዮ በሁለቱ ሀገራት
ግኑኝነት ዙሪያ መክረዋል።
 
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የሪፎርም ስራም የመከሩ ሲሆን፥ በዚህም ውቅት አሜሪካ ሀገሪቱ እያደረገች ላለችው የሪፎርም ስራ ድጋፏን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን ነው ያነሱት።
 
ከንግድ እና ኢንቨስትመንት አንፃር በተለይም የአሜሪካ የግል ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ የበለጠ መጥተው መዋእለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጠይቀዋል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም መጠበቅ እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
 
ይህንን ጥረቷንም አሜሪካ መደገፏን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውንም ነው አምባሳደር ሬድዋን የተናገሩት። 
 

በተመሳሰይ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያይተዋል።

በቆይታቸውም በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፥ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው መክረዋል።

አቶ ገዱ በዚህ ወቅት፥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ታሪከዊ እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር በመግለፅ፤  አሜሪካ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍም አድንቀወል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት እና አለቃቅ በተመለከተ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እያደረጉት ላለው ጥረትም አቶ ገዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በሚያደርጉት ውይይት አሜሪካ ከታዛቢነት ሚናዋ ልዩነቶችን ለማቀራረብ እያደረገች ያለውን ጥረት ያደነቁት አቶ ገዱ፥ ሶስቱ ሀገራት ከውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በበርካታ ጉዳዮች መግበባት ላይ ቢደርሱም በቀሪ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ለመድረስ ቀጣይ ስራ እንደሚጠይቅም በዚህ ወቅት አብራርተዋል።

አቶ ገዱ አክለውም ኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በተለይም የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰሩ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

የቀጠናውን ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት በተለይም በሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች፣ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደ ክልል እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎች በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በክልሉ ለምትጫወተው ቁልፍ ሚና አመስግነዋል።

አሜሪካ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗንና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ እንደሚመጣ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት አንጻር በቀሪ ጉዳዮች ላይ ሶስቱ ሀገራት ተወያይተው በእንጥልጥል ላይ ያሉ ጉዳዮችን ሊቋጩ እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፥ በቆይታቸው ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.