Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳትፎም ሆነ በፉክክር የህዝቡን የዴሞክራሲ ጥማት የሚያረካ እንዲሆን እንደሚሰራ ገለጹ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 25 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳትፎም ሆነ በፉክክር የህዝቡን የዴሞክራሲ ጥማት የሚያረካ እንዲሆን መንግስት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ 5ኛውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት በዚህ ዓመት የሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ እውነተኛ ዴሞክራሲ በተግባር የሚገለጽበት ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ምርጫዎች እውነተኛ ፉክክር ያልተካሄደባቸውና ፖለቲካዊ ምህዳሩም ተመጣጣኝ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይም ፓርላማው የተለያዩ ፓርቲዎች ሃሳባቸውንና ድምጻቸውን የሚያሰሙበትና እውነተኛ ውክልና የሚያገኙበት እንዲሆን እንደሚሠራም አስረድተዋል፤ ፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ እንዲኖር እንደሚሰራ በመጥቀስ፡፡

ሠላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ የሀገሪቷን ሰላም ለማስጠበቅ ምልዐተ ህዝቡን ያሳተፈ ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡

አያይዘውም የዴሞክራሲ መጎልበትና የሰለጠነ ፖለቲካን የሚያጠናክሩ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በሚደረገው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዜጎች ሰላማዊ መንገድና አቅጣጫን በመከተል የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል ሲሉም ጠቁመዋል።

የህግ የበላይነትን የማረጋጋጥ ስራ እና የታጠቁ ኃይሎች በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያበቃ የተጀመሩ ስራዎች መስመር እንደሚይዙም ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ ህዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ሃገራዊውን ሰላም የማረጋገጥ ስራ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ይሰራል ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ የማይወድቅባት ሃገር ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም የህግ የበላይነት እንዲኖር ተቋማትን የማጠናከር ሂደት አንደሚሰራ ጠቅሰው የዳኝነት ስርዓቱ በህግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲፈጽሙ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን በማዘመን ወደ ዲጂታል ለማሳደግ ይሰራል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ከትምህርት ተደራሽነት አንጻር ለትምህርት ጥራት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የትምህርት ስርዓቱ እንደሚሻሻልም አውስተዋል፡፡

የጤና ስርዓቱ ላይ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ መቀነስም ላይም በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያነሱት፡፡

ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንጻር ባለፈው ዓመት ስኬቶች መመዝገባቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ በዚህ ዓመት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል በንግግራቸው፡፡

ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘም በተያዘው በጀት ዓመት የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚከናወን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ የግድቡ ሁለት ተርባይኖችም ኃይል እንዲያመነጩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ የተያዘው አቋም አንድ ዓይነትና የማይለወጥ ነው፤ በማንኛውም ጫና የሚቀየር ነገር አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አካሄድ ትከተላለችም ነው ያሉት፡፡

ፕሬዚዳንቷ በተያዘው አመት የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ መቀነስ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ወረርሽኙ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ይሰራል ብለዋል ባደረጉት ንግግር፡፡

ከዚህ ባለፈም የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የኢኮኖሚውን ጤናማነት ማረጋግጥም የዚህ አመት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ለውጡን ተከትሎ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች መፈናቀሎችና ሞቶች አሳሳቢና በፍጥነት መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብሄራዊ መግባባት ላይ የተጀመሩ በጎ ጅምሮች እንዲቀጥሉና የወንድማማችነት ሀገራዊ እሴት እንዲዳብር ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡

በአዲሱ የስራ ዘመን ፈተናዎች ቢያጋጥሙም ፈተናዎችን በማሸነፍ ዕቅድን ለማሳካት መጣር እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ዜጎች ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.