Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጂቡቲ ቅርንጫፍን መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጂቡቲ የከፈተውን ቅርንጫፍ በትናንትናው እለት መርቀው ከፍተዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህን ጨምሮ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱላዚዝ መሃመድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እንዲሁም ሌሎች የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ በምረቃው ላይ፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጂቡቲ ቅርንጫፍ መከፈት የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።

እንዲሁም የሃገራቱን ህዝቦች የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክር እና የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በጂቡቲ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን የተሟላ የባንክ አገልገሎት እንዲያገኙ ያስችላልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በወጪና ገቢ ንግድ፣ መሰረተ ልማት፣ በውሃ እና በኤሌክትሪሲቲ ስትራቴጂካዊ እና ሁለንተናዊ ግንኙነት አላቸውም ብለዋል።

የቅርንጫፉ መከፈት በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ ሪፐብሊክ መካከል የሚካሄደውን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የሚረዳ መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ የገለፁት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.