Fana: At a Speed of Life!

ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ሰላም እና አንድነት ድጋፍ ትሰጣለች-ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት ለስራ ጉብኝት ጅቡቲ የገቡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም  ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጅቡቲ ከሁሉም ሀገራት ቀድማ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ ለሰጠችው በጎ ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግን ለማስከበር የሄደበትን ርቀት በተመለከተ ማብራሪያ ሰተዋቸዋል።

በተለይም የትግራይ ሕዝብ ከመከላከያ ጎን በመቆም ሰላም ፈላጊ መሆኑን ያስመሰከረበት ድል እንደሆነም ገልጸዋል።

የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል እያካሄደ ባለው ዘመቻ ለተቀዳጀው ድል የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳን እስማኤል ኦማር ጊሌ  ከጅቡቲ ጋር በደም፣ በቋንቋ እና በባሕል ብሎም በምጣኔ ሀብት ለተሳሰረችው ኢትዮጵያ “ሰላም እና አንድነት” ያላቸውን ሙሉ ድጋፍም መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ጦርነቱ ካለቀ በኋላ የሚኖረው የሀገር ግንባታ ምን መምሰል እንዳለበት እና በሕዝቦች መካከል ሰላምን ማስፈን እና እድገት ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባለ ብዙ መልኩ እና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ቀደም ከነበሩ ትብብሮች ባሻገር አዳዲስ ትብብሮችን ሊያካትት ይገባል ብለዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.