Fana: At a Speed of Life!

ፖሊስ በማይካድራ በተፈጸመው ወንጀል በርካታ ሰዎች ተገድለው 10 ሴቶች መደፈራቸውን እና ከ17 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፖሊስ በማይካድራ በተፈጸመው ወንጀል በርካታ ሰዎች ተገድለው 10 ሴቶች መደፈራቸውን እና 17 ሚሊየን 620 ብር የሚገመት በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገለጸ፡፡

ሴቶችን አስገድደው በማስደፈር እና በንጹሀን ዜጎች ግድያ በቀጥታ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ 36 ተጠርጣሪዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለሶስተኛ ጊዜ ቀርበዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ጃንቦ ብርሀነ፣ ሳጅን ርስቃይ በሪሁን እና ዳንኤል ገብሬ በሚል በሶስት በተደራጀ መዝገብ ተከፋፍለው ነው የቀረቡት፡፡

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ስራዎች አቅርቧል፡፡

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከህወሓት ጸረሰላም ቡድን ጋር በመቀናጀት የአማራ ብሄር ተወላጆችን በመለየት በርካታ ንጹሀን ዜጎች እንዲገደሉና የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡

በተፈጸመው ወንጀል ጉዳት የደረሰባቸው 59 ተጎጂዎችን የህክምና ማስረጃ ከጎንደር ሆስፒታል ማቅረቡን፣ የ20 ሰዎችን ምስክር ቃል መቀበሉን እና ከሳንጃ ሆስፒታል የ118 ሰዎች የጉዳት መጠን የህክምና ማስረጃ ማቅረቡን አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም በማይካድራ የ17 ሚሊየን 620 ብር መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረቡን እና የደረሰውን ጉዳት የሚያመላክት የምስልና የቪዲዮ ማስረጃ ማያያዙንም ገልጿል።

117 ሰዎች ተገድለው የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለማምጣት እና ተጨማሪ የሰው ምስክር ለመቀበል ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.