Fana: At a Speed of Life!

10 ስኳር ፋብሪካዎችን ለግሉ ዘርፍ የማዛወር ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 10 የስኳር ፋብሪካዎችን የሃገሪቱን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ለግሉ ዘርፍ የማዛወር ስራ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
 
መንግስት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ካሉት 13 የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ 10 ያህሉን ወደ ግል ይዞታነት እያዛወረ ይገኛል፡፡
 
የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ብሩክ ታዬ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ተቋማቱን ወደ ግል ይዞታነት የማዛወር ሂደት ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
 
በስኳር ፋብሪካዎቹ ወቅታዊ ቁመና ላይ ቴክኒካል ምዘና ማድረግ፣ ፋብሪካዎቹ ወደ ግል ይዞታነት በሚቀየሩበት ወቅት ሊኖር የሚገባው የስኳር ገበያ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ወይም የገበያ ስትራቴጅ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡
 
በቀጣይ ወደ ዘርፉ የሚገቡ የግል ተቋማትን መደገፍ የሚቻልባቸው አሰራሮች በእስካሁኑ ሂደት እንደተጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
 
ፋብሪካዎቹ በቀጣይ አቅም በተፈጠረላቸው ወቅት የሚኖራቸው ከባቢያዊ ተጽዕኖ ግምገማ ከግምት ስለመግባቱም ጠቁመዋል፡፡
 
የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግሉ የማዛወር ሂደቱ ሁለት አመት ቢሞላውም እስካሁን ወደ ግሉ ዘርፍ የተዛወረ ፋብሪካ የለም፡፡
 
ዶክተር ብሩክም ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እና በርከት ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ወሳኝ በመሆናቸው ሂደቱን ለመፈጸም ቁርጥ ያለ ቀን ማስቀመጥ እንደሚከብድ ያስረዳሉ፡፡
 
ወደ ዘርፉ መቀላቀል የሚፈልጉ ተቋማት በጉዳዮ ዙሪያ መከወን የሚጠበቅባቸው የፋይናንስ እና ሎሎች ዝግጅቶች ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
 
ይሁን እንጅ በተቻለ አቅም ሂደቱን በሚፈለገዉ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ማለቅ ያለባቸው ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
 
የስኳር ፋብሪካዎቹን የመግዛት ወይም በጋራ የመስራት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ለመለየት በተከናወነ የፍላጎት መጠየቂያ ጥናትም እስካሁን 30 የሚደርሱ ተቋማት ዘርፉን መቀላቀል እንደሚፈልጉ ታውቋል ነው ያሉት፡፡
 
የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ይዞታነት በማሽጋገሩ ሂደት የሚመለከታቸውን የመንግስት ተቋማት የሚያማክር ድርጅት የመቅጠሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ዶክተር ብሩክ የገለጹት።
 
መተሃራ፣ ፊንጫ እና ወንጅ ስኳር ፋብሪካዎች ለጊዜው በመንግስት ስር ይቆያሉ ተብሏል፡፡
 
ወልቃይት፣ በለስ 1 እና 2 ፣ ከሰም እና ሌሎች ቀሪ ፋብሪካዎች በመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ግል ይዞታነት ይሸጋገራሉ ተብሏል፡፡
 
በአወል አበራ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.