Fana: At a Speed of Life!

12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርት ፌስቲቫል መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርት ፌስቲቫል በጃን ሜዳ መካሄድ ጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መሰረት በመሆናቸው ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የባህል ስፖርቶችን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማግኘት እንደሚቻል ገልጸው ፤ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ ስፖርቶች ባለቤት ብትሆንም በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ተጠቃሚነቷ ዝቅትኛ ሆኗል ብለዋል።

በቀጣይ ግን ህዝባዊነቱን ማስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ በማድርግ ከዘረፉ ተጠቃሚ ለመሆን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፤ ባለፉት ዓመታት የባህል ስፖርት ተገቢውን ጥበቃና ትኩረት ባለመሰጠቱ ሊጎለብት አልቻለም ብለዋል።

በመሆኑም መሰል ፊስቲቫልና ውድድሮች መካሄዳቸው ዘርፉን ለማስተዋወቅና ህዝቡን ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አድማሱ፤ የባህል ስፖርትን ለማሳደግ በማሰብ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በከፍለ ከተሞች የባህል ስፖርት ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዛሬው እለት የተጀመረው ፊስቲቫልና ውድድርም በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ውድድር የተሻሉ ስፖርተኞችን ለማሳተፍ ያግዛል ነው የተባለው።

12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርት ፌስቲቫልና ውድድር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም በ10 የባህል ስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን 10 የባህል ስፖርት አይነቶች ለውድድር ይቀርባሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.