Fana: At a Speed of Life!

13ኛው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 13ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ በዓል ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም “ሰንደቅ ዓላማችን ለሰላማችን፣ ለአብሮነታችንና ለሃገራዊ ብልጽግናችን!” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገለጸ፡፡

ቀኑ በየዓመቱ የተለያየ መሪ ቃል እየተቀረፀለት በፌደራል፣ በክልልና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በዋናነት ስለሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ውክልና እና ትርጓሜ እንዲሁም አዋጁን የሚያብራሩ ሰነዶች እየቀረቡ በሰፋፊ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች ሲከበር መቆየቱ ተገልጿል፡፡

ዘንድሮም ለ13ኛ ጊዜ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደር ከተሞች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና ወቅታዊ ለውጡን በሚያስቀጥሉ እንዲሁም ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር በተገናዘበ አግባብ በየተቋማቱ በመላው ሃገሪቱ የሚከበር ይሆናል ነው የተባለው፡፡

የበዓሉ ማጠቃለያ ስነ ስርዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ስነስርአት ይከናወናል፡፡

በተጨማሪም በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ-መሃላ በመፈጸም የሚከበር ሆኖ በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ በኤምባሲዎች እና በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች ውስጥ በተመሳሳይ ሰዓት የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ስነ-ስርዓት እንደሚከናወንም ይጠበቃል፡፡

የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 ዓ/ም አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር መደንገጉ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.