Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ18ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 18ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
 
የምክር ቤቱ ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
 
1. ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የተወያየው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው ረቂቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነው። ኮቪድ-19 ክትባትም ሆነ መድሃኒት የሌለው፣ በፍጥነት የሚዛመት እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን በመገንዘብ፤ የቫይረሱ ስርጭት በተለያዩ ሃገራት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያጠቃ እና ለብዙ ሺዎች መሞትም ምክንያት መሆኑ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር በተለመደው የጤና አጠባበቅ ዘዴ እና አካሄድ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አዳጋች በመሆኑ፥ በሃገራችን ተጨባች ሁኔታም የቫይረሱ ስርጭት እና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን እያስከተለ የሚገኝ ሲሆን ለነዚህ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኗል። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል ሥርዓት በአንቀጽ 93 ተደንግጓል። በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ ከሚሆኑ ሁኔታዎች አንዱ “የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት” መሆኑም ሰፍሯል። የኮቪድ-19 የሕዝብን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ከመሆኑም በላይ የአለም ጤና ድርጅት አለም አቀፍ ወረርሽ መሆኑን ማወጁን ተከትሎ ከ70 የማያንሱ አገሮች ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ህዝቦቻቸውን ለመታደግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥተዋል። በአገር ደረጃ ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ሲባል ከተለመደው አሠራር ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል። ምክር ቤቱን በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ጥቂት ማስተካከያዎችን በማከል ከዛሬ 29/07/2012 ዓም ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስራ ላይ ባለበት ወቅት በመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93(2(ሀ)) መሰረት በአስቸኳይ ለምክር ቤቱ እንዲላክ ጭምር ተወስኗል።
 
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር ጋር የተደረጉ 3 የብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡። የመጀመሪው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ41 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ሲሆን፥ ሁለተኛው ለአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ክፍለ አህጉራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ54 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ነው። ሶስተኛው ለሁለተኛው የኢትዮጵያ የዕድገት እና የተወዳዳሪነት የልማት ፖሊሲ ፋይናንስ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 1346 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፥ ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች 0 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የእፎይታ ያላቸው እና በረጅም ጊዜ ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆናቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትሉት ጫና የሌለ መሆኑን እና የኮቪድ 19 ቫይስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚደረገው አገራዊ ርብርብ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሙሉ ድምጽ አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.