Fana: At a Speed of Life!

29ኛው የግንቦት 20 በዓል  ተከብሮ ዋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 29ኛው የግንቦት 20 በዓል በዛሬው እለት በመላው ሀገሪቱ  ተከብሮ ውሏል።

የግንቦት 20 የድል መታሰቢያ በዓልን በማስመልከትም በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መድፍ ተተኩሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም 29ኛው የግንቦት 20 በዓልን በማስመልከት በትናንትናው እለት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ግንቦት 20 የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት አንዱ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን ህይወታቸው ሰውተዋል ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

የግንቦት 20 ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሆኑን በመልዕክታቸው አንስተዋል።

ግንቦት ሃያን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቀኑን የምናስበው በግንቦት ሃያ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደፊት እየሄድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበትም በማለት አሳስበዋል፡፡

ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረምም ነው ያሉት፡፡

ሀገራቸው በሁሉም መመዘኛ ግንቦት ሃያን አልፋ ግንቦት ሃያ አንድንም ተሻግራ ወደ ግንቦት 22 መድረስ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የግንቦት ሃያ ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው፤ የብልጽግና ጎዳናችን ዓላማ ግንቦት ሃያ ላይ ቆሞ ግንቦት አሥራ ዘጠኝን እያሰቡ መኩራራት ሳይሆን ሀገራችንን ወደ ግንቦት 22 ማስፈንጠር ነው ሲሉም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ማለትም ሀገራችን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን መድረስ ወደነበረባት የላቀ ደረጃ ማድረስ መሆኑን አስታውሰዋል።

የግንቦት 20 የድል መታሰቢያ በዓልን ሰናከብር በተባበረ ክንድ ከግንቦት ሃያ የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደርግ ምጡቅ ሥርዓት ለመገንባት ቃላችን የምናድስበት እና ወደ ላቅ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል ብለዋል በመልዕክታቸው።

በተያያዘ ዜና 29ኛውን የግንቦት 20 የድል መታሰቢያ በዓልን በማስመልከት የተለያዩ ሀገራት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላልፈዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በላኩት የደስታ መግለጫ ደብዳቤ እንኳን አደረሳችሁ ብሏል።

ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን አክለውም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም እምነታቸውን ገልፀው፤ መልካሙን ሁሉ ተመኝተዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ልኡል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማንም ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በላኩት መልእክት የእንኳን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን፥ ለኢትዮጵያ መንግስት እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ ከሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ የሆኑት  ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አልመክቱም እንዲሁም የአቡዳቢ ልኡል አልጋ ወራሽና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጦር አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በላኩት የደስታ መግለጫ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

በተጨማሪም የኦማን ሱልጣን ሀይታም ቢን ታሪክም ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በላኩት የደስታ መግለጫም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.