Fana: At a Speed of Life!

38ኛው የኢጋድ የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 38ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡

በጂቡቲ በተካሄደው ጉባኤ ኢጋድ በቀጠናው ሃገራት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡
በጉባኤው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ገለጻ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ዘመቻው ህገመንግስቱንና የሃገሪቱን አንድነት በመጠበቅ መረጋጋት ማምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ኢጋድ በበኩሉ ህዳር 19 ቀን ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል አስተማማኝ በሆነ መልኩ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ የተደረሰውን ስምምነት አድንቋል፡፡

ከሱዳን ጋር በተያያዘም በሃገሪቱ ከሁለት ዓመታት በፊት የተከሰተውን የህዝብ አብዮት ተከትሎ የታየውን የዴሞክራሲ የሽግግግር ሂደት በማድነቅ በደቡብ ሱዳን ጁባ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አወድሷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንዲሰሩና የሱዳን መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሽግግር ጊዜ ህግ አውጭ ምክር ቤት እንዲመሰርቱም ጠይቋል፡፡

ኢጋድ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ የሃገሪቱ መንግስትና ፓርቲዎች በተሻሻለው የደቡብ ሱዳን የግጭት የውሳኔ ሃሳብ ትግበራ ላይ ያሳዩት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የሃገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች ያቋረጡትን የሰላም ድርድር እንዲቀጥሉና ከዚህ ቀደም የደረሷቸውን ስምምነቶች ተፈጻሚ ያደርጉ ዘንድም ጠይቋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሀገር ምስረታው ላይና የአስተዳደር መዋቅሩ የስልጣን አሰጣጥ ሂደት እንዲሁም የሰላም ውይይት ዳግም መጀመሩ የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስም በሃገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሪክ ማቻር ላይ ምንም ዓይነት የጎዞ እገዳ አለማስተላለፉን ገልጿል፡፡

ሶማሊያን በተመለከተም የፌደራል መንግስቱና የየግዛት አስተዳዳሪዎች ስምምነት የሚደነቅ መሆኑን አንስቷል፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) የሚታገዘው የጸጥታ ሃይል አልሻባብን በመዋጋት ረገድ እያሳየ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በመግለጫው አውስቷል፡፡

ሶማሊያ ከሶማሌላንድ ጋር የጀመረችውን ውይይት አድንቆ የቀጠናው መንግስታትም ለውይይቱ መሳካት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም ነው ያነሳው፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም ኢጋድ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የቀረጸውን ስትራቴጂ በመደገፍ የአውሮፓ ህብረት ጊዜውን የጠበቀ ድጋፍ በማድረጉ አመስግኗል፡፡

በተጨማሪም ወረርሽኙን ለመመከት የኢጋድ ሴክሬታሪያት የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ከአባል ሃገራት ሚኒስትሮች ጋር በመቀናጀት እና ጥረቶችን በማሳደግ ላሳየው ትጋት ምስጋና ችሮታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.