Fana: At a Speed of Life!

4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዛሬ በይፋ ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ዛሬ በይፋ ይጀመራል።

በመርሃ ግብሩ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ፥በዚህ ዓመት በአጠቃላይ በአራት ዓመቱ መርሐ ግብር ለመምታት የታቀደው 20 ቢሊየን ችግኞች የመትከል ግብ እንደሚሳካ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በዓየር ንብረት ለውጥ እጅጉን ተፅዕኖ እየደረሰባት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት በሀገር ደረጃ የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመግታት ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ መርሃ-ግብር ነውም ብለዋል፡፡

“ዛሬ የምንዘራው ዘር ነገ ፍሬ እንደሚያፈራ እና ለትውልድም እንደሚተላለፍ አንጠራጠርም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የዓየር ንብረት ለውጡን ለመግታት እንዲሁም የውሃ እና የዓየር ብክለት ለመቀነስ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ደረቃማ አካባቢዎች ዓመታዊ የዝናብ መጠናቸው እንዲጨምር ብሎም የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት እንዲቀንስ ሀገራችንን በርትተን አረንጓዴ ማልበስ አለብንም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስቷል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በየዓመቱ ሚሊየኖች ችግኝ በመትከል እንደሚሳተፉም ያመላከቱ ሲሆን በሀገሪቷ ተሥፋፍተው በተቋቋሙ በርካታ ችግኝ ጣቢያዎች ከ183 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መፍጠር እንደተቻለም ነው ያነሱት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ÷ ከከባቢ ዓየር ጋር የተስማማ ዘርፈ-ብዙ የብልፅግና መሠረት መጣሉም ተጠቁሟል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ላይ የታየው መነሳሳት በግብርናው ዘርፍ ላይም ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ መድገም እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ የተገኘው ልምድም ለአፍሪካውያን እና ለተቀረው የዓለም ክፍል ትምህርት ሊሆን የሚችል ስኬት እንደሆነም በመግለጫው ተወስቷል፡፡

በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር መላ ኢትጵያውያን በነቂስ ወጥተው ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአፍሪካውያን በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ቀጣይነት እና ስኬት የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.