Fana: At a Speed of Life!

4ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ችቦ በመቐለ ተለኮሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ 4ኛው ዙር የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ቡድን ችቦ የመለኮስ ስነስርዓት በመቐለ ከተማ ተካሄደ፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን የቶኪዮ 2020 ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ የትግራይ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፥ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ በአትሌቲክስ 10 እና በብስክሌት 1 ስፖርተኞችን ክልሉ ማስመረጡን አንስተዋል።

አያይዘውም ክልሉ ስፖርትን በማጠናከርና የበኩሉን በመወጣት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ጎን እንደሚሆን በማረጋገጥ ለቡድኑ መልካም እድል ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን የቶኪዮ 2020 ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፥ ትግራይ ክልል ብዙ ስፖርተኞች ማፍራቱን ጠቅሰው፥ በቀጣይ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶች ማፍራት ይገባል ብለዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ አቶ አባዱላ በቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያን በብቸኝነት በብስክሌት ስፖርት ለምትወክለው ሰላም ዓመሃ ከህዝብ የተበረከተልኝ ነው ያሉትን የአንገት ሀብል ሸልመዋል።

በአዲስ አበባ የተለኮሰው የኦሊምፒክ ችቦ ጉዞውን ቀጥሎ በቀጣይ 5ኛው በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል የሚለኮስ ሲሆን፥ የክልሉ አፈ ጉባኤ አቶ ላክደር ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር ከአቶ ታይዶር ቻምባንግ ጋር በመገኘት ችቦውን ተረክበዋል።

በዚሁ ወቅት አፈጉባኤው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቡድንን እንደ ክልል በተገቢው መንገድ እንደሚደፉ ቃል ገብተዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.