Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ  ከ1 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከ1 ሚሊየን ላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚ ሊደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኢንሹራንስ በሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ወረዳዎች ከ1 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ቤት ለቤት ምዝገባ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አማካኝነት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ፣ የመድሃኒት አቅርቦት እና ሌሎች አስፋላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡

ከጥቅምት ወር ጀምሮ ቤት ለቤት በተካሄደ ምዝገባ ከ180 ሺህ በላይ አባዎራዎች እና እማወራዎች የተመዘገቡ ሲሆን አገልግሎት ለመስጠት በእቅድ ከተያዘው አንድ ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች 83 ከመቶ በላይ መመዝገብ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም 55 ሺህ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ አባወራዎች እና እማወራዎች በከተማ አስተዳደሩ ወጪ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ዮሃንስ አመልክተዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪዎች 350 ብር አመታዊ ክፍያ በመክፈል በሁሉም የመንግስት የጤና ተቋማት ነጻ የቤተሰብ ህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ሀላፊ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኢንሹራንስ አግልግሎት በ2009 ዓ.ም በተወሰኑ ወረዳዎች አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ሲሆን እስከአሁን ከ446 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በመላ ሀገሪቱ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.