Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ከህወሓት ወንጀለኞች ጋር ድርድር አይቀመጥም – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ከህወሓት ወንጀለኞች ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አን ሊንዴ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በውይይታቸው በዋናነት መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ትኩረት አድርገው መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አቶ ደመቀ መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ካለው ህግን የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞም ሊኖር ስለሚችል ድርድር፣ በትግራይ ክልል ስላለው የመገናኛና የሃይል አቅርቦት እንዲሁም መንግስት እየወሰደ ካለው ህግን የማስከበር እርምጃ ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉና ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ገለጸ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ከህወሓት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማለሳለስ የሄደበትን ርቀት በተመለከተ ለሚኒስትሯ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

መንግስት ህወሓት በአዲሱ የመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲሳተፍ የሰጠውን በቂ ጊዜና እድል ቡድኑ ሳይጠቀምበት መቅረቱንም ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ቡድኑ ከስልጣን ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ ህገ ወጥ አካሄዶችን በመከተልና ፅንፈኛ ቡድኖች በማደራጀት፣ በማሰማራትና በገንዘብ በማገዝ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲያሰማራ መቆየቱንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በህገ ወጥ መንገድ በማን አለብኝነት ክልላዊ ምርጫ ማካሄዱንም ጠቅሰዋል።

ቡድኑ በሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጥቃት መንግስት በጁንታው የህወሓት ቡድን ላይ እርምጃ እንዲወስድ እንዳስገደደው ጠቅሰው፥ መንግስት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርድር እንዲደረግ ያቀረበውን ሃሳብ እንደሚያደንቅም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን መንግስት ከህወሓት ወንጀለኞች ጋር ድርድር እንደማይቀመጥ ጠቅሰው፥ ጁንታውን ለህግ በማቅረብ ህገ መንግስቱን እንደሚያስከብርም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አቶ ደመቀ አያይዘውም መንግስት አሁን ላይ ለተፈናቀሉና ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን በመጥቀስም፥ በጁንታው ድርጊት የተስተጓጎሉ የመገናኛ እና የባንክ አገልግሎቶችን ዳግም ለማስጀመር እየሰራ ስለመሆኑም አውስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.