Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት የህዝቡ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩና የመንግሥት ትብብር ያስፈልጋል – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት የህዝቡ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የፌዴራሉ መንግሥትና የመከላከያ ሠራዊት ትብብር ወሳኝ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አስታወቀ።

መርማሪ ቦርዱ በትግራይ ክልል በሚያደርገው የመስክ ምልከታ በቁጥጥር ስር ያሉ እስረኞችን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችንና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እየጎበኘና ከማህበረሰቡም ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ነው የገለጸው።

ቦርዱ በመልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ በሽሬ ከተማ ከጊዜያዊ አስተዳደሩና ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የሽሬ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ገብረ ፃዲቅ የህግ ማስከበሩ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ የተዘረፉ ንብረቶችን የማስመለስ፣ ህዝቡን የማረጋጋትና ከቀዬቸው የተፈናቀሉ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በየኬላው ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን በጸጥታ ስጋት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እንዲመለሱና ድጋፍ እንዲያገኙም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሓት ጁንታ ውድመት ካደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች መካከል የመብራትና ቴሌ አገልግሎት በሽሬ እስካሁን አለመጀመሩን ጠቅሰው፤ የመልሶ ግንባታ ሥራው እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

በተለይ የከተማው ነዋሪ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ እየጠየቀ መሆኑንም አንስተዋል።

በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ በበኩላቸው “በክልሉ የመልሶ ማቋቋም ስራ ህዝቡ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ መከላከያ ሠራዊትና መንግሥት የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ የጦር መሳሪያ ያላቸው፣ በጫካም ሆነ በበረሃ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ካሉ ትጥቃቸውን ለሚመለከተው አካል አስረክበው ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።

መርማሪ ቦርዱ በህዝቡና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚቀርቡ ድጋፍ፣ እገዛና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚመለከተው አካል እንዲፈታ ክትትል እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.