Fana: At a Speed of Life!

5 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለው የአባያ ሃይቅ ክፍል በእምቦጭ ተወሯል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አባያ ሀይቅ በእምቦጭ አረም መጠቃቱን የደቡብ ክልል የአከባቢና ደን ባለስልጣን የብዘሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት አስታወቀ።

የዳይሬክቶሬቱ ኃላፊ አቶ መላኩ ባፋ ፥ እምቦጭ አረም የአባያ ሀይቅን በስፋት እያጠቃ መሆኑን ገልፀው፥ አረሙን ለማጥፋት የሚያስችሉ ስራዎችና ሙከራዎች በሰው ጉልበትና በመሳሰሉት ለመግታት ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡

በዚህም በሀይቁ ላይ ያለውን ብዘሃ ሕይወት በማይጎዳ መልኩ አረሙን የማጥፋት ዘመቻ ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፥በአሁኑ ወቅት ከሀይቁ 5 ሺህ ሄክታር የውሃው አካል በእምቦጭ አረም መጠቃቱ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ጥበቃ ሀዋሳ ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አለምነህ ሙጬ በበኩላቸው፥አረሙ በፍጥነት ካልተወገደ ብዘሃ ሕይወቱን ብቻ ሳይሆን ከሀይቁ በሚገኝ ገቢ የሚተዳደሩትን በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጭምር ገቢ በማሳጣት ሊጎዳ እንደሚችል ገልፀዋል።

እንደ ደሬቴድ ዘገባ የእንቦጩ መስፋፋት ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተባብሮ ለመስራት እንዲያስችል ከስምጥ ሸላቆ ተፋሰስ ባለስልጣን ጋር በጥምረት ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ሃይቁ በውስጡ ከ54 በላይ ብዘሃ ሕይወትን የያዘው የአባያ ሀይቅ በዓመት ከ4 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ የማምረት አቅም ያለውና ዓዞን ጨምሮ በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ያሉ የዱር እንስሳትም የህልውናቸው መሰረት መሆኑ ይነገራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.