Fana: At a Speed of Life!

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተናገሩ።

ሚኒስትሯ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ በተደራጀ መልኩ ግጭቶች እንዲባባሱ የሚሰሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ተናግረዋል።

የተቋማቱን ችግር ለመለየት አጣሪ ቡድን ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ባደረገው ምርመራ ግጭቱን ለማባባስ የተደራጀ እንቅስቃሴ ስለመፈጸሙ አረጋግጧል።

በዚህም ተቋማቱ በራሳቸው ሴኔት ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃን መውሰድ ጀምረዋል ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ሚኒስትሯ።

በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተዘጉበት ምክንያትም ችግሮችን ለመፍታት የቀውስ አስተዳደር ስርአትን ለመተግበር በመወሰኑ ነው ብለዋል።

ይህም በአጭር ጊዜ የጸጥታ ችግራቸውን በመፍታት ወደ መማር ማስተማሩ እንዲመለሱ ያደርጋልም ነው ያሉት።

ባለፈው አመት በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ እርምጃን በመውሰድ ተቋሙን ማረጋጋት መቻሉንም አስታውሰዋል።

ተቋማቱ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ሌላ የግጭት ምክንያት በመሆናቸው ከአካባቢው አመራሮች ጋር የቅንጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

መንግስት የፌደራል ፖሊሶችን በግቢው የጸጥታ ስራ ላይ በማሰማራት የመማር ማስተማሩን ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.