Fana: At a Speed of Life!

ሙዚቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል – ጥናት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙዚቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ አንድ ጥናት አመላከተ።

በብሪታንያ የተደረገው ጥናት ሙዚቃ እያዳመጡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ውጤታማ እንደሚያደርግ ያመላክታል።

ጥናቱ ከ25 እስከ 65 እድሜ ባላቸው ሰዎች ላይ የተደረገ ሲሆን፥ ፈጠን ያለ እርምጃ እና በቀን ለተወሰኑ ደቂቃዎች የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎችን አካቷል።

በጥናቱ የተካተቱት ሰዎች ለረጅም ሰዓታት ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው የሚሰሩ ሲሆን፥ በሁለት ምድብ ተከፍለው በሙዚቃ የታጀበ ፈጣን እርምጃ እና የእግር ጉዞ አድርገዋል።

በዚህም የአንደኛው ቡድን አባላት በየቀኑ ለ30 ደቂቃ ያክል ሙዚቃን እየሰሙ ፈጣን እርምጃ እየተራመዱ ተገምግመዋል።

በአንጻሩ በሌላኛው ቡድን ውስጥ ያሉ ተሳታፊዎች ደግሞ በቀን 10 ሺህ እርምጃዎች ያለ ሙዚቃ እንዲራመዱ ተደርጓል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለቱም ቡድን ውስጥ ለውጥ ቢታይም፥ ሙዚቃን እያዳመጡ ለ30 ደቂቃ ፈጠን ያለ እርምጃ በየቀኑ የሚራመዱት የተሻለ ውጤታማ ሆነዋል ነው ያሉት።

በዚህኛው ቡድን ውስጥ ያሉ አባላት የነበራቸው የስብ ክምችት በ2 ነጥብ 4 በመቶ ሲቀንስ፥ በቀን 10 ሺህ እርምጃ ያለሙዚቃ የተራመዱት ደግሞ በ1 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ቀንሷል።

ከዚህ ባለፈም ከሙዚቃ ጋር ለ30 ደቂቃ እርምጃ የተራመዱት የደም ግፊታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ መታየቱንም ጠቅሰዋል።

ይህም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሙዚቃ አጅቦ መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ማሳያ ነው ብለዋል አጥኝዎቹ።

በተጨማሪም በፍጥነት የሚራመዱ ሰዎች ከማይራመዱት ጋር ሲነፃጸሩ በ24 በመቶ ረጅም እድሜ የመኖር እድል አላቸው ነው የተባለው።

በሌላ በኩል የሚያነቃቃ ወይም ፈጠን ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ የልብ ህመምን ለማስወገድ እና ለአዕምሮ ጤንነት ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.