Fana: At a Speed of Life!

6 ሚሊየን ህፃናትን ከመቀንጨር ለመታደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ፕሮግራምን ውጤታማ በማድረግ በመቀንጨር የተጠቁ 6 ሚሊየን ህፃናትን ለመታደግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሙከራ ምእራፍ ትግበራ የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈጻጸም ግምገማ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ፥በኢትዮጵያ የምግብና የስርአተ ምግብ ዋስትና ባለመረጋገጡ በርካታ ህፃናት ለመቀንጨር ተጋልጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ያሉ 6 ሚሊየን ህፃናት ለመቀንጨር የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በተከዜ ተፋሰስ ላይ በሚገኙ የአማራና የትግራይ ክልሎች በ40 ወረዳዎች እድሜያቸው ከሁለት አመት በታች ያሉ ህጻናት በአሳሳቢ የመቀንጨር ችግር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በስርአተ ምግብ እጥረት የቀነጨሩ ህፃናት እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በትምህርት አቀባበላቸው፣ አካላዊና አዕምሮአዊ እድገት ላይ ተፅእኖ በማሳደር ለራሳቸውም ሆነ ለሃገራቸው አስተዋፅኦ እንዳያበረክቱ ያደርጋቸዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትም የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትን በመተግበር በሃገር አቀፍ ደረጃ የመቀንጨርን ችግር በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረስ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ባለፉት ሁለት አመታትም መንግስት እና አጋር ድርጅቶች የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት አመት የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ግብ ለማሳካት 477 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመደበው በጀትም በፍጥነት ለውጥ በሚያመጡ የግብርና፣ የትምህርት፣ የእናቶችና ህጻናት ጤና አጠባበቅ፣ በውሃ አቅርቦት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች ልማቶች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።

የተመደበው ሃብት ለታለመለት አላማ እንዲውልም የሚመለከታቸው አስፈፃሚዎች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሙከራ ትግበራ ላይ የነበረው ፕሮግራም ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር የ15 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ መነደፉን ጠቅሰዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የፌደራል ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ በበኩላቸው፥ በፌዴራል እና በክልል መስሪያ ቤቶች የሚፈፀሙ ተግባራትን መረጃን መሰረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ስርአት በመዘርጋቱ የፕሮግራሙ የትግበራ ምእራፍ ስኬታማ እያደረገው መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮግራሙ በዚህ ዓመት በአማራና በትግራይ ክልሎች ለሚገኙ 40 ወረዳዎች የትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የሚያስችል በጀት ተመድቦ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የመረጃ ስርአቱን ለማጠናከር ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የስልክ መሰረተ ልማት በማስፋፋትና መሰረተ ልማቱ ባልተዘረጋላቸው 721 ቀበሌዎች ደግም በሳተላይት አማካኝነት ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮግራሙ በሙከራ ትግበራ ምእራፉ ላይ በፍላጎትና በሃብት አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲሁም የቀበሌዎችየመንገድ መሰረተ ልማት ያለመሟላት ችግር አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.