Fana: At a Speed of Life!

64 ሚሊየን ብር የሚገመት ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ ተያዘ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ደብቆ ኬላ ጥሶ ለማለፍ የሞከረው አሽከርካሪ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የጉምሩክ እና በአካባቢው በነበሩ የኦሮሚያ ክልል የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ፖሊስ ገለፀ።

ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ11:30 በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ቦረና ከተማ ዶሎ በር ኬላ ትዮታ ደብል ፒክአፕ ላንድ ክሩዘር ከነጋሌ ከተማ ወደ ሶማሌ ክልል ለመሄድ ቀጥታ በጉምሩክ ኬላ በኩል መጥቶ ለፍተሻ ሲያስቆሙት ፊቃደኛ ባለመሆን በኬላው ጎን ባለው የእግረኛ መንገድ በመጠቀም ጥሶ ለማለፍ ሲሞክር ለማስቆም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ጥይት ቢተኩሱም ሳይቆም በማምለጥ ላይ እያለ የጉምሩክና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ለነበረው ኮማንድ ፖስት መረጃውን በፍጥነት በማስተላለፍ ዶሎ በር አካባቢ በሚገኘው የእርዳታ እህል ማራገፊያ አየር ማረፊያ አካባቢ የኦሮሚያ የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሏል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲፈተሽም 16 ኪ.ግ ወርቅ የተገኘ ሲሆን አሁን በገበያ ላይ ባለው ዋጋ በብር ሲተመን 64 ማሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑ ተረጋግጧል።

ከነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅም በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ከተማ በሚገኘው የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ መጋዘን ገቢ እንደተደረገ የፌደራል ፓሊስ ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.