Fana: At a Speed of Life!

የአሽከርካሪ እና ተሳፋሪዎችን ጡንቻ የሚያነቃቃ የተሽከርካሪ ወንበር ተሰራ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃጓር ላንድ ሮቨር ኩባንያ አሽከርካሪዎች መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት ጡንቻዎቻቸውን ማነቃቃት የሚችል መቀመጫ ወንበር መፈብረኩን አስታወቀ።

ወንበሩ አሽከርካሪዎች ወይም ተሳፋሪዎች ከመቀመጥ ብዛት የሚያጋጥማቸውን የጡንቻ መስነፍ በመቀነስ ጡንቻቸውን የሚያነቃቃ ነው ተብሏል።

መቀመጫ ወንበሩ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ተሳፋሪዎች ተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው የእግር ጉዞ እያደረጉ መሆኑን እንዲሰማቸው በማድረግ፥ የሰውነት ጡንቻቸውን በማነቃቃት ለረጅም ጊዜ ከመቀመጥ የሚከሰትን የጤና ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ነው የተባለው።

የአሁኑ ፈጠራ በዓለም ላይ ያለውን የጋዝ ልቅት፣ አደጋ እና የትራንስፖርት መጨናነቅ ዜሮ ለማድረግ የተያዘው የዜሮ መዳረሻ ፕሮጀክት አካል ነው ተብሏል።

የጃጓር ላንድ ሮቨር የህክምና ክፍል ሃላፊ ዶክተር ስቴቬ አሌይ የፕሮጅክቱ ዋና አላማ የደንበኞችና ሰራተኞችን ጤንነት እና ደስተኛነት መጠበቅ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሽከርካሪ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ተፅዕኖ ለመቅረፍ የኢንጅነሪንግ ሙያተኞችን በመጠቀም የወደፊቱን ወንበር (መቀመጫ) ፈብርከናል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የሚሆነው የዓለም ህዝብ ብዙውን ጊዜ ተቀምጦ የሚያሳልፍ ሲሆን ይህም በጡንቻ፣ ዳሌ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ለሚከሰት ጉዳት ምክንያት ነው።

ምንጭ፡- autocar.co.uk/

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.