Fana: At a Speed of Life!

76 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከኬንያ ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 76 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በፈቃደኝነት ከኬንያ መመለሳቸው ተገለፀ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፥ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን በኬንያ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ናቸው።

ስደተኞቹን የመመለስ ስራው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ እና በኬንያ መንግስታት ትብብር እየተሰራ ነው ተብሏል።

በትናንትናው እለት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት 76 ስደተኞች ከሶማሌ ክልል የወጡ እና እስከ 12 ዓመታት በስደት የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

ከተመላሾቹ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፥ በስደት ተወልደው ያደጉ ልጆችም ይገኙበታል ነው የተባለው።

በቀጣይ ወራትም በርከት ያሉ ፈቃደኛ ስደተኞች ከካኩማ እና ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኬንያ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለዓመታት የቆዩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከ3 እስከ 40 ዓመታት የቆዩና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎታቸውን የገለፁ 2 ሺህ 281 የሚሆኑ ስደተኞች ለሀገራቸው እንዲበቁ የጉዞ ሰነዶችን እየሰጠ መሆኑንም ነው በወቅቱ የገለፀው።

ይህን ተከትሎም ከካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 85 እንዲሁም ከዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ደግሞ 2 ሺህ 196 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጉዞ ሰነድ ተዘጋጅቶላቸዋል ነው የተባለው።

በካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 10 ሺህ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 7 ሺህ ገደማ በድምሩ 17 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.