Fana: At a Speed of Life!

81ኛው አርበኞች የድል በዓል ተከበረ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 81ኛው የአርበኞች የድል በዓል አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት እናትና አባት አርበኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በ81ኛው የአርበኞች የድል በዓል ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡

የድል ቀን ከዛሬ 81 አመት በፊት ሚያዝያ 27 ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ተዋድቀው ፋሽስት ጣልያንን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ድል ያበሠሩበት ዕለት ነው።

ፋሽስት ጣልያን አድዋ ላይ የተከናነበውን ሽንፈት ለመበቀል ለ40 አመታት ሲዘጋጅ ቆይቶ የመርዝ ጭስና ሌሎች በጦርነት ህግ ያልተፈቀዱ መሳሪያዎችን በመጠቀም በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ በሶስት አቅጣጫ ወረራ ማካሄዱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያውያንም እንደ ወራሪው ዘመናዊ መሳሪያ ባይኖራቸውም ባላቸው አቅም ለስምንት ወራት በጽናት የተዋጉ ሲሆን፥ ወራሪው አዲስ አበባና ሌሎች ጥቂት ከተሞችን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ተረጋግቶ እንዳይገዛ በከተሞቹ ዳር በመሆን እረፍት ነስተውት ቆይተዋል።

እናትና አባት አርበኞች፣ የሀይማኖት መሪዎች ወጣቶችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በልጆቿ ደም የጸናችና ነጻነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ከፋሽስት ጣልያንና ከከባድ መሳርያዎቹ ጋር ለአምስት አመታት ተዋድቀዋል።

ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓመተ ምህረትም በዱር በገደል ኢትዮጵያውያን የተዋደቁለትን ሰንደቅዓላማ አጼ ኃይለሥላሴ በቤተ መንግስታቸው የሰቀሉበት በአዲስ አበባ ከተማም ሰንደቁ የተውለበለበበት ታላቅ የድል ቀን ነው።

በየአብቃል ፋሲል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.