Fana: At a Speed of Life!

900 ሚሊየን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘላቸው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ 900 ሚሊየን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘላቸውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ስምምነት ከአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው በመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የሚገነባውን የተቀናጀ የመስኖና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንዲሁም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አሥር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታን ለማሠራት መሆኑ ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው÷ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአማራ ክልል በዋግኽምራና በደቡብ ወሎ ዞን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዋግኸመራ የሚገነባው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት 488 ሚሊየን ብር የተመደበለት ሲሆን የበጀት ምንጩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታም በአንድ ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ ከ17ሺህ በላይ ሰዎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ዶክተር ማማሩ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውምበደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የሚገነባው የተቀናጀ መስኖና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
የገፀ ምድር ውኃን ተጠቅሞ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸው÷ከክልሉ መንግስት በተመደበ 410 ሚሊየን ብር ግንባታው እንደሚካሄድም ዶክተር ማማሩ ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ውኃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመነ ፀሐይ÷ ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሠርቶ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት፡፡
አያይዘውም ድርጅቱ የሕዝቡን በውኃ የመልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.