በጅማ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በዛሬው እለት በጅማ ከተማ ስታዲየም የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ።
ሰልፉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን፣ መላውን የለውጥ አመራር እና ብልጽግናን ለማበረታታት ያለመም ነው።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰዎች ባላቸው ፖለቲካዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ሊሰደቡ አይገባም ብለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ አቃፊና ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር ለዘመናት የኖረ ነው ሲሉም ሰልፈኞቹ ገልፀዋል።
ነዋሪዎቹ በማከልም “ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላማችንን አስጠብቀን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን” ነው ያሉት።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት ህብረተሰቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ አድንቀዋል።
በዚህ ረገድ የጀመረውን ስራ ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ የአጋሮ ከተማ እና ዙሪያዋ ነዋሪዎችን ያሳተፈ የድጋፍ ሰልፍ በዛሬው እለት በአጋሮ ከተማ ተካሂዷል።
በሙክታር ጠሀ