የሀገር ውስጥ ዜና

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር ኢሌኒ ገ/መድህን ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰረዘ

By Meseret Awoke

November 30, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዶክተር ኢሌኒ ዘውዴ ገ/መድህን ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰረዝ መወሰኑን አስታወቀ፡፡

ዶ/ር ኢሌኒ ሰሞኑን የዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል ተብሎ ይጠራ በነበረው ድርጅት አማካኝነት በድብቅ በተዘጋጀ የበይነመረብ ስብሰባ ላይ ሙያዊነትን ያልጠበቀ፣ አድሏዊ፣ የአንድን ቡድን ፍላጎት ብቻ ያንጸባረቀ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችንን ዋና ዋና እሴቶች የሚፃረር ሀሳብ በማራመዳቸው ዩኒቨርሲቲው ለዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ የሰጠውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በድጋሚ ሲያጤን እና ሲመረምር እንደቆዬ አስታውቋል፡፡

በዚህም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011፣ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 4 እና በዩኒቨርሲቲያችን የሴኔት ደንብ አንቀጽ ቁጥር 6 ንዑስ አንቀጽ 16 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ለዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ ገ/መድሕን ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰረዝ መወሰኑን አሳውቋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ለዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ ገ/መድኅን የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በማቋቋምና በመምራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ (Honorary Degree of Human Letters (DHLitt)) የሰጣቸው መሆኑን አስታውሷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በወቅቱ የክብር ዶክትሬቱን የሰጣቸው የህብረተሰባችንን አኗኗር እና የሀገራችን የውጭ ንግድ ስርዓት እንዲሻሻል ባበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ እና ለወደፊቱም በተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ልክ ሀገራችን ያለአድሎና በእኩልነት እንዲያገለግሉ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችንን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ ነበር ብሏል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!