ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Alemayehu Geremew

December 03, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት፣ ባሕላዊ ዕሴቶች እና የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር ተስማሙ፡፡

አገራቱ የኮቪድ ወረርሽኝን በጋራ ለመከላከልም እንደሚተባበሩ ነው የጠቆሙት፡፡

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የውጪ ጉዳዮች ኮሚሽን ዳይሬክተር ያንግ ይቺ፥ በቀጣዩ ዓመት ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 30 ኛ ዓመት ያከብራሉ ብለዋል፡፡

አያይዘውም በጥምረት ልማት ላይ ለመስራት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ እቅድ ነድፈው እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡

ቻይና በቀጠናው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ከሌሎችም የአካባቢው አገራት ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ነው ያንግ ይቺ የጠቆሙት፡፡

የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሳህ ሁን በበኩላቸው፥ አገራቸው ከቻይና ጋር እያደገ ለመጣው ግንኙነት ቦታ ትሰጣለች ብለዋል፡፡

በቀጣይም በበርካታ መስኮች የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ቤጂንግ ለምታስተናግደው የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክ ከጎኗ ሆና ድጋፍ እንደምታደርግም አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ለቀጠናው ዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ከቻይና ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናት ማለታቸውን ሺንዋ ዘግቧል፡፡