የሀገር ውስጥ ዜና

የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ በተዛባ ሁኔታ መዘገባቸውን ቀጥለዋል  

By Mekoya Hailemariam

December 04, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ በተዛባ ሁኔታ መዘገባቸውን ቀጥለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ ረፋዱን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምዕራባውያኑ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ በመሬት ላይ ካለው እውነታ በተቃራኒው መዘገብ መቀጠላቸውን ነው የገለፁት።

ለአብነትም ቢቢሲ “ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነቱን ለማባባስ ትምህርት ቤቶቿን ዘጋች” በሚል ርዕስ በገጹ ያወጣው ዘገባ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ የደረሰ ሰብልን በዘመቻ የመሰብሰብ የቀደመ ባህል የነበረ ሲሆን፥ ተማሪዎችም በጋራ በመሆን ትምህርት ዘግተው የአርሶ አደሩን ሰብል በህብረት ሲሰበስቡ ቆይተዋል።

ይህንን የሀገሪቱን ባህል እና እውነታ ሳይረዳ በተዛባ ሁኔታ የቀረበውን የቢቢሲ ዘገባ በመኮነን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪ ቢለኔ ስዩም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ቢቢሲ በርዕሱ ያመላከተው ሃሳብ ሆን ተብሎ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት የወጣ መሆኑን ገልጸው፣ ትምህርት ቤቶች የተዘጉት ተማሪዎች ያልተሰበሰቡ የዘማች አርሶ አደሮች ሠብል ለመሰብሰብ ጊዜ እንዲያገኙ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳላትና በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ርብርብ የሚያስፈልግ በመሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ አግባብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፥ ቢቢሲን “የሐሰት አባት” በማለት የወጣውን አሳሳች ርዕስ አውግዘዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሌሎች የትምህርት ዘርፉ አካላት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሣምንት እንዲዘጉ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

በውሳኔውም  2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከህዳር 27 እስከ ታሕሣሥ 3 ቀን 2014 ዝግ ሆነው ያልተሰበሰቡ የዘማች የደረሱ ሠብሎችን በመሰብሰብ፣ ገንዘብ በማዋጣት፣ ደም በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀት ሚናቸውን ይወጣሉ ተብሏል፡፡