Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ የኢትጵያን አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ተላልፈዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ማስተላለፍ መቻሉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው በተለያዩ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በአልጄሪያ እየተካሄደ ያለው የሚኒስትሮች ጉባኤ ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀው፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያም ጉባኤውን በሊቀመንበርነት እየመራች እንደምትገኝ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በመድረኩ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን የተለያዩ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነትና ጫና ያልተገባ መሆኑን አስረድተዋል።

መሰል ጣልቃ ገብነትም የአፍሪካን ሰላም ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑንም አብራርተዋል ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በኮሪያ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ማስከበር ጉባኤ ላይም በንቃት መሳተፏን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም ሰላምና ጸጥታን ለመስከበር ፍቃደኛ መሆኗንና ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡በዚህም እንደምትቀጥል ነው ያስተያወቁት፡፡

በተያያዘም የሰላም አስከባሪ ሃይል የሚያዋጡ ሀገራት በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉት መደበኛ ያልሆነ ጦር የማስፈር ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ እና መቆም እንዳለበት ማሳሰባቸውንም ነው ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ የተናገሩት፡፡

 

በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አቶ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ፤ የህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ባካሄደባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል፤ ንብረትና መሰረተ ልማቶች አውድሟል ብለዋል፡፡

ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ነን ባዮች፥ የሽብር ቡድኑ የፈጸማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ማንሳት አይፈልጉም፣ አሁንም በዝምታ ማለፍ መርጠዋል ነው ያሉት፡፡

በተቃራኒው መንግስት የሰብዓዊ መብት እንደጣሰ አድርገው ክስ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡

እንዲሁም በአካባቢው እርዳታ የሚሹ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው፥ መንግስት የረድኤት ድርጅቶች ለተረጂ ወገኖች እርዳታ የሚያደርጉበትን መንገድ እያመቸቸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሜሪካ “በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል” በሚል ኢትዮጵያን ለመወንጀል ለወራት ሲዘጋጅ የነበረው ረቂቅ አዋጅ በሀገሪቱ ብሄራዊ መከላከያ ፍቃድ ህግ መሰረዙን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
ይህ ሰነድ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ የፈለጉ ወገኖችም ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የህግ መሰረት ለመሰጠት አስበው እንደነበር ነው ያመለከቱት።

ሆኖም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትና ዜጎች ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ሰነዱ ሳይፀደቅ ተሰርዟል። ለዚህም አበርክቷቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በፌቨን ቢሻው

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.